ግብርለሀገር ልማት ያለውን ፋይዳ በመረዳት ግብራችንን በአግባቡ እየከፈልን ነው…የሀድያ ዞን ሞዴል ግብር ከፋዮች

468

ሆሳእና መጋቢት 6/2011 ግብር ለሀገር ልማትና እድገት ያለውን ጥቅም በመረዳት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ መሆናቸውን የሀድያ ዞን ሞዴል ግብር ከፋዮች ተናገሩ፡፡

በሃዲያ ዞን ሌሞወረዳ ሀምብቾ ቀበሌ ነዋሪና ሞዴል ግብር ከፋይ የሆኑት አባ ገዳ በቀለ ሀጂሮ እንዳሉት ያለግብር በአካባቢው መሰረተልማት መሟላት እንደማይቻል በማመን ግብራቸውን በውዴታ ከፍለዋል፡፡

“ግብር መክፈል ለምንጠቀምበት መሰረተ ልማት ድጋፍ ማድረግ በመሆኑ ሁሉም ሰው ግብሩን በመክፈል ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” ብለዋል።

የእህል ነጋዴው አባገዳ በቀለ በበኩላቸው በዓመት እስከ 25 ሺህ ብር ግብር ያለቀስቃሽ እንደሚከፍሉና ግብር ለሀገር ልማት አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። 

” ግብር ለሀገር እድገት የጀርባ አጥንት በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ያሉት ደግሞ በሆሳዕና ከተማ ናረሞ ቀበሌ የካፌና ሬስቶሪንት ባለቤት አቶ አዲስአለም መላክ ናቸው፡፡

“አገልግሎት ሰጪ በመሆናችን መብራት፣ ውሃና መሰል መሰረተ ልማቶችን ከመንግስት ለማግኘት ግብሬን በተገቢው መንገድ እየከፈልኩ ነው” ብለዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት ከ100 ሺህ ብር በላይ ግብር ለመንግስት መክፈላቸውንም ተናግረዋል።

ሁሉም የሚጠበቅበትን ግብር መክፈሉ ከሀገሩ የሚፈልገውን የልማት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሚያግዝ መሆኑን በመረዳት ኃላፊነቱን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።

“ግብር መሰወር ለሀገር እድገት እንቅፋት በመሆኑ ከሀገር ልማት ተጠቃሚ ለመሆን ግዴታችንን መወጣት አለብን” ሲሉም ተናግረዋል።

ሀገር እንድታድግ የሚፈልግ ማንኛውም ዜጋ በራሱ ተነሳሽነት ግብር መክፈል አለበት” ያሉት ደግሞ በሌሞ ወረዳ መስቢራ ቀበሌ የሚኖሩት አቶ ታገሰ ሽጉጤ ናቸው፡፡

የደረጃ “ለ” ግብር ከፋይ መሆናቸውንና ከምግብ ቤት ስራቸው በዓመት ከቫት ገቢ ውጪ 45 ሺህ ብር ግብር እንደሚከፍሉ ተናግሯል፡፡

የእናቶችንና ህጻናትን ሞት በመቀነስና በጤናው ዘርፍ ውጤታማ ሥራ ለመስራት ግብርን በአግባቡ መክፈል ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

የሀድያ ዞን ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ንጉሴ ማሞ በበኩላቸው በዞኑ 108 ሞዴል ግብር ከፋዮች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ሞዴል ግብር ከፋዮች የተመረጡት የክፍያ መመዝገቢያ ማሽን በአግባቡ በመጠቀማቸው፣ ግብራቸውን ሳይሸሽጉ በወቅቱ በመክፈላቸው፣ የትርፍና ኪሳራ መግለጫቸውን በማሳወቃቸውና የግብር ግዴታቸውን ተግባራዊ በማድረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“ሞዴል ግብር ከፋዮቹ ቫትና የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ በአግባቡ ለተጠቃሚው ህብረተሰብ በማድረስ፣ ያለቀስቃሽ ግብራቸውን በመክፈልና ግብርን ባለመሰወር ለሀገር ልማት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆናቸው አርአያ ያደርጋቸዋል” ብለዋል፡፡

ሞዴል ግብር ከፋዮችን የሚከተሉ ሌሎች ግብር ከፋዮችን በማፍራት ገቢን በሚፈለገው መጠን ለመሰብሰብ በንቅናቄ የተጀመረው ሥራ መጠናከሩንም አቶ ንጉሴ አመልክተዋል፡፡

እንደእሳቸው ገለጻ በዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት 686 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን ባለፉት 7 ወራት 340 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል፡፡

በቀሪው ጊዜ ንቅናቄውን በማቀላጠፍ ከዕቅድ በላይ ለማሳካት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡