የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል በኢትዮጵያ ውጤታማ ቆይታ አድርገዋል… የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

79

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2011 የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ የነበራቸው የሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት የተሳካና ውጤታማ እንደነበር የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

በተለያዩ አገሮች በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማስፈታት ወደአገር ቤት እንዲመለሱ የማድረግ ጥረቱ እንደቀጠለም ተጠቁሟል።

የፕሬዚዳንቱን ጉብኝት ጨምሮ በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ዛሬ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

እንደ አቶ ነቢያት ገለጻ፤ ፕሬዚዳንት ማክሮን በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ማጠናከር የሚያስችሉ ስምምነቶች ተፈርመዋል።

ፕሬዚዳንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል ምክክር አድርገዋል።

የፈረንሳይ መንግስት የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያን ለመጠገን የሙያና የገንዘብ ድጋፍ፣ የመከላከያ ሃይል ዓቅም ለማጎልበት በተለይም አየር ሃይልና ባህር ሃይልን ለማጠናከር እንዲሁም ለተለያዩ የልማት ስራዎች የሚውል የገንዘብ ድጋፍና ብድር ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት መፈረሙን አስታውሰዋል።

''በአጠቃላይም የኢትዮ-ፈረንሳይ ግንኙነትን ለማጠናከር ፕሬዝዳንት ማክሮን በኢትዮጵያ የነበራቸው ጉብኝት የተሳካና ውጤታማ ነበር'' ያሉት አቶ ነብያት ጉብኝቱ ሁለቱ አገሮች የነበራቸውን ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያያዘም ከትላንት ጀምሮ በኢትዮጵያና በቱኒዝያ መካከል የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በቱንዚያ እየተካሄደ መሆኑን አቶ ነቢያት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን ልኡክ የመሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ ሁለቱ አገሮች በባህልና ቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ፣ በሴቶችና ቤተሰብ ፕሮግራም፣ በሙያና ስልጠና መስክ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት እንደተፈራረሙ አስታውቀዋል።

እነዚህንና ቀደም ሲል የተፈረሙ ስምምነቶችን ተግባራዊ በሚሆኑባቸው ጉዳዮች ዙሪያም ትኩረት ሰጥተው ምክክር ማድረጋቸውን ነው የገለጹት ቃል አቀባዩ።

ባለፈው እሁድ መጋቢት1 ቀን 2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት በሆነው ቦይንግ 737 ኢቲ 302 ላይ በደረሰው የመከስከስ አደጋ ከሚኒስቴሩና ከአየር መንገዱ የተወጣጣ ግብረ ኃይል አቋቁሞ መረጃ የመስጠት ሚናውን እየተወጣ እንደሆነም በመግለጫቸው አመልክተዋል።

አሁንም ከአደጋው ጋር የተያያዙ ቴክኒካዊ መረጃን በሚመለከት ከአየር መንገዱ የተወጣጡ ባለሙያዎች መረጃን በመቀበልና ለኤምባሲዎችና ለተለያዩ አገሮች የአደጋውን ይዘት የሚዳስስ መረጃ እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአደጋው ማግስት መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ወደ ሚኒስቴሩ በመጥራትና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚመለከታቸውን የስራ ኃላፊዎች በማሳተፍ ዝርዝር መረጃ እንደተሰጠ ገልጸዋል።

ከ50 በላይ የአገሮች መሪዎች በአደጋው ዙሪያ የሃዘን መግለጫ መልእክቶቻቸውን መላካቸውንም ጠቁመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያለመኖሪያ ፈቃድ በተለያዩ አገሮች በእስር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ከኤምባሲዎችና ቆንጽላ ጽህፈት ቤቶች ጋር በመተባበር ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን በሚመለከትም በሳምንታዊ መግለጫቸው ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጂዳ በሚገኘው ቆንጽላ ጽህፈት ቤት በኩል ከሳዑዲ አረቢያ መንግስትና ከዓለምአቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር ያለመኖሪያ ፍቃድ የነበሩ 447 ኢትዮጵያውያን መጋቢት 4 እንዲመለሱ መደረጉን አስታውሰዋል።

በቀይ ባህር በኩል በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የገቡና የተያዙ 1 ሺህ 800 ኢትዮጵያውያንም በአራት ዙር ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ሚኒስትቴሩ፣ ከብሄራዊ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከታንዛንያ መንግስት ጋር በመተባበር 50 ኢትዮጵያውያን 'ታንጋ' ከሚባል የታንዛኒያ እስር ቤት እንዲለቀቁና በትናንትናው እለት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉንም አብራርተዋል።

ከ450 በላይ የሚሆኑና በተለያዩ የታንዛኒያ እስር ቤቶች የሚገኙ ዜጎችንም እንዲሁ ለማስለቀቅ ከታንዛኒያ መንግስት ጋር እየተደረገ ያለው ድርድርም ተጠናክሮ ቀጥሏል ይላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም