አገራዊ አንድነትን ለመፍጠር ልዩነቶች ላይ መግባባት ይገባል-ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች

77
አዲስ አበባ ግንቦት 23/2010 በኢትዮጵያ አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ውጤታማ  ይሆን ዘንድ በሀገሪቷ ያለውን ዲሞክራሲ ማጠናከር እንደሚገባ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ። በሀገሪቷ ያለውን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋት በአሁኑ ወቅት የተጀመሩት እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ፓርቲዎቹ አሳስበዋል። የአንድነት፣ የሰማያዊ፣ የኢዴፓና የመኢብን ፓርቲ አመራር አባላት ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የህዝቡን የዴሞክራሲና የፍትሃዊነት ጥያቄዎች በአግባቡ በመመለስ ሀገሪቷ የምታልመውን አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠር ራዕይ እውን ማድረግ ይቻላል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በሀገሪቷ አዎንታዊ የኢኮኖሚ ለውጦች ዙሪያ መግባባት መፈጠሩን የሚያሳዩ እውነታዎች ቢኖሩም በተለይ በፖለቲካው ረገድ ተመሳሳይ ሁኔታ ለመፍጠር ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ የፓርቲዎቹ መሪዎች ተናግረዋል። አቶ ትዕግስቱ አወሉ የአንድነት ሊቀመንበር እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች  አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ  ማህበረሰብ ለመፍጠር ያላቸውን  ሚና ሲገልፁ “ፖለቲካል ኢኮኖሚ ነው በራሱ፤ ምክንያቱም ከኢኮኖሚ ስንነሳ ወደ ፊት ወደ ሽግግር እናመጣለን ስንል እኛም ድርጅታችን እንደዚያ ነው የሚያምነው ወደ ኢንዱስትሪ መር ነው ወደዚያ ትራንስፎርም ለማድረግ የግድ ኃይል ወሳኝ ነው። ሁለተኛ ነገር የውጪ ምንዛሬን ከማስገኘት አንጻርም አስተዋጽኦ አለው። አሁን በምንሰራበት ሁኔታ ይህ ትልቅና ሁላችንንም የሚያግባባ ነው። የሚያግባባ ነው የምለው ለምንድን ነው? በራስ ኢኮኖሚ በህዝቡ አስተዋፅኦ የሚሰራና የኔነት ስሜት ያለው ኢኮኖሚ ግንባታ ስለሆነ ነው። '' ልጅ መስፍን ሺፈራው  የመኢብን ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ''አንድ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገው እንቅስቃሴ ህገ መንግስታዊ መሰረት ያለው ነው፤  ላለፉት አመታት ገዢው ፓርቲም ሲያቀነቅነው የነበረና በህብረተሰቡም በተፎካካሪ ፓርቲዎችና በኢህአዴግ መካከል ሲነሱ የነበሩ እንቅስቃሴዎች ናቸው። በሂደት ከሚደረገው እንቅስቃሴ አንፃር የህዝብ ፍላጎት አለ፤ የፓርቲዎችም ጥያቄ አለ። ገዢው ፓርቲም እየሰራባቸው የመጣባቸው ነገሮች አሉ።አንድ ሊያደርጉን የሚችሉና ለአገራዊ እይታ ግንባታ ጠቃሚ ናቸው ተብለው የሚታሰብባቸው በርካታ ስራዎች እንደተሰሩ እናምናለን'' አቶ የሺዋስ አሰፋ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር በሰጡት አስተያየት ''እንደ አገር በሃይማኖት ፣ በባህል  መከራና ደስታን በማሳለፍ ማንም ሊነጥለው ያልቻለ የፖለቲካ የኢኮኖሚና የባህል ማህበረሰብ አለ። '' አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ''እነዚህ  በተለያዩ ቦታዎች የሚደረጉ መሰረተ ልማቶች የጋራ መግባባትና አንድነትን ለመፍጠር እድል ይሰጣሉ። ሰው በኢኮኖሚና  በቴክኖሎጂ እየተሳሰረ በሄደ ቁጥር ለኢኮኖሚ መግባባቱ እድል ይሰጣል ግን ያም ቢሆን የፍትሃዊነት ጥያቄ በተለያየ መልኩ ይነሳበታል'' ብለዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አመራሮች አክለውም ሰላምና ልማት የጋራ መሆናቸው የሚያግባባ ቢሆንም ለሁሉም እኩል እድል መሰጠት አለበት ብለዋል። ከህገ-መንግስቱ ጀምሮ ያሉና በህዝቡ መካከል የጋራ መግባባትን ይሻሉ ተብለው የሚታሰቡ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ፓርቲዎቹ ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት ህዝቡ እያቀረባቸው ላሉት የተለያዩ ጥያቄዎች አፋጣኝ መልስ መስጠትም የጋራ መግባባት ለመፍጠር የሚደረገውን እንቀስቃሴ የበለጠ ውጤታማ ያደርገዋል ብለዋል። ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ ባልተመለሱ ጥያቄዎች ሳቢያ ተቃውሞውን ሲያሰማ ቆይቷል፤ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ችግሮቹን መፍታት ወሳኝ ነው ሲሉም የፖለቲካ አመራር አካላቱ ገልፀዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ እንደሚሉት ዲሞክራሲውን በማጠናከር አመቺ የፖለቲካ ድባብ ሲፈጠር እንደዚሁም ኢኮኖሚያዊ እድገቱን በማፋጠን የሁሉንም ዜጋ የልማቱ እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ሁኔታ ሲመቻች ሀገሪቷ ወደ ተሻለ ብሄራዊ መግባባት ትሸጋገራለች የሚል እምነት አላቸው። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ ግን የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በመንግስት የተጀመሩት እንቅስቃሴዎች የአንድ ወቅት ሥራዎች ሳይሆኑ በዘላቂነት ሊቀጥሉ እንደሚገባም አሳስበዋል። የጋራ መግባባት ያልተደረሱባቸውን ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ላይም መፍትሄ ለመስጠት የጋራ ውይይት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል። አቶ ትዕግስቱ አወሉ የአንድነት ሊቀመንበር ''አሳታፊ የፖለቲካ ሁኔታ መፈጠር አለበት። ሌላው ህገ መንግስቱ ላይ በራሱ የጋራ መግባባት መፈጠር አለበት። በራሱ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ማለት ነው። ይህንን ለማምጣት የግድ ብሄራዊ መግባባት መኖር አለበት። ብሄራዊ መግባባት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ የሚኖረው መድረክ ማለት ነው።” አቶ የሺዋስ አሰፋ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር''መነጋገር ያስፈልጋል ፣ እኛ እንደ መፍትሄ  የምናስቀምጠው ሁሉን አቀፍ ውይይት ያስፈልጋል ፤ውጪ ያለ ውስጥ ያለ የታጠቀ ያልታጠቀ የተመዘገበ ያልተመዘገበ ብሎ ሳይሆን ሁሉም ለዚህ አገር መፍትሄ አመጣለሁ የሚል ሰው በሙሉ ጥሪው ይደረግለት፤ በዚያ ጥሪ መሰረት ሃሳብ አለኝ የሚል በአንድ ተወካይም ሆነ በሁለት ሃሳቡ ይምጣ '' ልጅ መስፍን ሺፈራው  የመኢብን ፕሬዝዳንት ''ቆም ብሎ ኢህአዴግ ባለድርሻ አካላት ነን ከሚሉት ጋራ ራሱን መፈተሽ አለበት ። የሚፈትሽውም  ደግሞ ህገ መንግስቱን ነው፤ አሁን በአካል ካለው ሰው ጋር ነገሮችን ማዋሃድ ነው፤ ቁጭ ብሎ መፈተሽ ማየት ነው ፣ ይሄ አሰርቷል አላሰራም ህገመንግስቱን መፈተሽ ሲቻል ነው'' አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ''ለብሄራዊ መግባባት መሰረት የሆኑ መደላድሎች መሰራት አለባቸው፤ ያለፈው ሶስት አመት ቀውስ ያስተማረን ነገር ቢኖር በዋናነት ከዚህ በኋላ በየራሳችን መንገድ እየሄድን አገር ከማፍረስ ውጪ ሌላ ውጤት ማምጣት እንደማንችል ነው ያሳየን፤ ኢትዮጵያ የምትባል አገር የሁላችንም አገር ነች ብለን ሁላችንም የራሳችንን አስተዋፅኦ ለማድረግ ብሄራዊ መግባባት ላይ መስራት አለብን፤ ከልዩነት ይልቅ አንድነታችን ላይ ማተኮር መቻል አለብን'' አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሀገሪቷ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ የሚል እምነት እንዳላቸው የገለጹት የተፎካካሪ ፓርቲዎቹ አመራር አካላት በእርሳቸው አመራር በአሁኑ ወቅት የተጀመሩት የለውጥ ውጥኖችና አርምጃዎች ለሀገሪቷ ትልቅ ተስፋ ናቸው ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም