የ4ኛው ዙር የሕዝብና ቤት ቆጠራ ዝግጅት መጠናቀቁን ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ

526

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2011 በተያዘው ወር መጨረሻ የሚጀመረው 4ኛው ዙር አገር አቀፍ ሕዝብና ቤት ቆጠራ ዝግጅት መጠናቀቁን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት አበራሽ ታሪኩ ከሌሎች የኤጀንሲው የስራ ኃላፊዎች ጋር ዛሬ በጉዳዩ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም በይፋ የሚጀመረው 4ኛው ዙር የሕዝብና ቤት ቆጠራ የካርታ ስራ፣ የመረጃ ቋት ማሳደግ፣ የሰው ኃይል ማሟላት፣ ሎጂስቲክስና ስልጠና ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

”ለ1 ሺህ 600 የአሰልጣኝ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸው፤ ከየካቲት 26 ጀምሮ እስከ መጋቢት 8 የሚቆይ የቆጣሪና ተቆጣጣሪ ስልጠናዎች በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ 25 ቅርንጫፎች ለ8 ሺህ 600 ባለሙያዎች በመሰጠት ላይ ነው” ብለዋል።

በቆጠራው በአጠቃላይ 180 ሺህ የሰው ሃይል እንደሚሰማራ ገልጸው፤ የዘንድሮ ቆጠራ ከዚህ በፊት ከነበሩት ሶስት ቆጠራዎች በተለየ የመረጃ አሰባሰብ በዲጅታል ወይም በታብሌት ኮምፒተሮች እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ለቆጠራው የተመለመሉ ሰዎች መምህራን፣ የጤናና የግብርና ባለሙያዎች ሲሆኑ አካላዊ ብቃት፣ ስነ ምግባርና ሌሎች መስፈርቶች እንዳሉበት ጠቁመዋል።

ለመረጃ ስብሰባ ከሚሰራጩ 180 ሺህ ታብሌቶች መካከል 90 በመቶዎቹ የመረጃ መሰብሰቢያ መተግበሪያ እንደተጫነላቸው ገልጸው፤ ቀሪዎቹም በጥቂት ቀናት ውስጥ ሶፍትዌሩ ተጭኖላችው እንደሚሰራጩ ገልጸዋል።

የቆጠራ መረጃዎችን የያዙት መተግበሪያዎች በኤጀንሲው ከፍተኛ የአይሲቲ ባለሙያዎች የተዘጋጁና በልዩ ልዩ መረጃ መሰብሰቢያ ሲያገለገሉ የቆዩ ቢሆንም ከአሁኑ ቆጠራ ግዙፍነት አንጻር ከአሜሪካ የቆጠራ ቢሮ የባለሙያ ድጋፍ መገኘቱን ጠቁመዋል።

በሶፍትዌር ዝግጅቱ የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) እንዳለበት የሚገለፀው ጉዳይ ከእውነት የራቀ መሆኑን ገልጸው፤ ኢንሳ በመረጃው ቋት ደህንነት ጥበቃ እንጂ በሌሎች ቴክኒካል ጉዳዮች ኃላፊነት እንደሌለው አብራርተዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ለቆጠራ ስራ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በጀት እንደነበረው የገለጹት ወይዘሪት አበራሽ፤ አሁን ላይ ለሚደረጉ ስራዎች በገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር በኩል 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለክልሎች መከፋፈሉን ገልጸዋል።

በወቅቱ ግምት ውስጥ ያልገቡ ስራዎችን ለማከናወን ደግሞ ተጨማሪ የበጀት ጥያቄ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡን በማመልከት በጀቱ በቅርብ እንደሚለቀቅ እምነታችውን ገልጸዋል።

የሚሰበሰበውን መረጃ ተዓማኒነት በተመለከተም ከፌዴራል እስከ ወረዳ የራሱ የቆጣሪ ተቆጣጣሪዎች እንዳሉት በመጠቆም፣ መረጃው ከተሰበሰበ በኋላ ቆጣሪው የሞላውን መረጃ ከታብሌት ኮምፒተሮች የሚያሳይበትና ከተቆጣሪ ጋር የሚፈራረምበት ወረቀት መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበርም የተሰበሰበው መረጃ ከተቆጠረበት ታብሌት በቀጥታ ወደ ማዕከል የመረጃ ቋት የሚገባበት ስርዓት ተዘጋጅቷል።

በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ባለው አለመረጋጋትና የዜጎች መፈናቀል ባለበት ስፍራ ቆጠራውን ለማካሄድ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የተፈናቀሉ ዜጎች ወደነበሩበት ቦታ ከተመለሱ በቋሚ መኖሪያቸው፣ ካልተመለሱም ባሉበት አካባቢ ስለመፈናቀላችው የሚያሳይ አስፈላጊው መረጃ ተሞልቶ በተጠለሉበት ስፍራ እንደሚቆጠሩ አመልክተዋል።

ብሔርና ሃይማኖትን በተመለከተም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ማንኛውም ብሄር ብሔረሰብ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት በተወስደ ዝርዝር መሰረት በተሰጣቸው ኮድ እንደሚቆጠሩ ተናግረዋል።

”ተቆጣሪው ከሁለት ብሄር በመወለድም ሆነ በሌላ ምክንያት ‘ብሔሩን’ ለመመለስ ከተቸገረ ዘር፣ ትውልድ፣ ነገድና ጎሳውን በማብራራት በተቀመጡ ኮዶች እንዲካተት ይደረጋል” ብለዋል።

የጥያቄው ዓላማ የብሄር ስብጥር መረጃ ለመሰብሰብ በመሆኑና ‘ኢትዮጵያዊ’ የሚለው የዜግነትን እንጂ የብሔር ማንነት ስለማይገልጽ ‘ኢትዮጵያዊ’ በሚል የቆጠራ ኮድ አልተዘጋጀም ብለዋል።

ኃይማኖትን በተመለከተም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ኃይማኖቶች ተለይተው ኮድ መሰጠቱን፤ ከ18 ዓመት በታች ከሆኑት በስተቀር የቤተሰቡ አባላት ግላዊ ሃይማኖታቸውን በማሳወቅ እንዲሞላ ለቆጣሪዎች ስልጠና መሰጠቱን ተመልክቷል።

4ኛው ዙር ቆጠራ ከመጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለ20 ቀናት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

በቆጠራው የሚገኘውን ውጤት፣ ሌሎች የመረጃ ግብዓቶችን በመጠቀም የሕዝብ ብዛት ትንበያ እንደሚሰራ ተጠቅሷል።