በአማራ ክልል የአካባቢ ብክለት ለመቀነስ የወጣውን አዋጅ ለማስፈጸም ዝግጅት እየተደረገ ነው

600

ባህርዳር መጋቢት 5/2011 በአማራ ክልል ወደትግበራ የገቡ ፕሮጀክቶች እያደረሱ ያሉትን የአካባቢ ብክለት ለመቀነስ የወጣውን አዋጅ ለማስፈጸም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በክልሉ ምክር ቤት የፀደቀውን ይህንኑ አዋጅ ቁጥር 181/2003 ለማስፈፀም የወጣውን መመሪያ ለባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅ በእንጅባራ ከተማ  የተዘጋጀ መድረክ ተካሄዷል።

የክልሉ  የአካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ በመድረኩ እንዳሉት በክልሉ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል  በየዓመቱ  የተለያዩ ፕሮጀክቶች ወደትግበራ ይገባሉ።

ፕሮጀክቶቹ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሰነድ አዘጋጅተው ወደትግበራ ቢገቡም የተፅዕኖ ግምገማ ሰነዱን ችላ ብለው የሚለቁት በካይ ፍሳሽ ኬሚካል በአካባቢው ስነ-ምህዳርና በህብረተሰቡ ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደትግበራ እየገቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶች አብዛኞቹ ተፈጻሚነት  ላይ ክፍተት ስላለባቸው  ለችግሩ መባባስ አስተፅኦ ማድረጉን ጠቁመዋል።

” የትኛውም የልማት ፕሮጀክት ሀገር ይጠቅማል በሚል እሳቤ ህዝቡን ሳናወያይና ሳናማክር ወደተግባር በመግባት ዜጎችን ለጉዳት የምንዳርግበት አሰራር ሊታረም ይገባል “ብለዋል።

የአካባቢ ጥበቃና ልማትን በመጣጣም ተፈጻሚ ካልሆነ  ማህበራዊ ፍትህ እንዲዛባና ዘላቂ ልማት አደጋ ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል።

የወጣውን አዋጅ ወደመሬት የሚያስነካ መመሪያ ባለስልጣኑ በማዘጋጀትም በአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ አተገባበር ላይ አተኩሮ ይህንን ለባለድርሻ አካላት በማስተዋወቅ ችግሩን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።    

የወጡ አዋጆች እንዲተገበሩ እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊና የአማራ ክልል ምክር ቤት የግብርናና አካባቢ ጥበቃና ውሃ ሃብት ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ወርቁ ዓለሙ ናቸው።

እሳቸው እንዳሉት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሳያካሂዱና የሰነድ ዝግጅት ሳያደርጉ ወደትግበራ የሚገቡ በርካታ ፕሮጀክቶች በአካባቢና በህብረተሰቡ ጤና ላይ እያደረሱ ያለው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም።

የክልሉ ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ምስራቅ ተፈራ   “መመሪያው የህዝቦችን ምቾት ፣ዕድገትና ዘላቂነት ለማረጋገጥ የህብረተሰቡን ጤና ለማስጠበቅ ወሳኝ ነው “ብለዋል።

በባለስልጣኑ የአካባቢ ልማት ዳይሬክተር አቶ አበባው አባይነህ በበኩላቸው “በመመሪያው ክልከላ የሚደረግባቸው የፕሮጀክት ባለቤቶች የአካባቢ ባለሙያዎች ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ ሲሄዱ የሚከለክሉ ከሆነ ፕሮጀክቱ እንዲታገድ ይደረጋል “ብለዋል።

እየደረሰ ያለውን ችግር ለመፍታት መመሪያውን ለማስተግበር ከአቃቤ ህግ፣ ከፖሊስና ከሌሎችም  ቢሮዎች የተወጣጣ ግብረ ኃይል መቋቋሙንም አስታውቀዋል።

ከክልል እስከ ወረዳ የተቋቋመው ግብረ ኃይልም በመመሪያው በተቀመጡ ጥፋቶች ልክ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሰነዱ መሰረት በማይተገብሩ ፕሮጀክቶች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ያደርጋል። 

በክልሉ በየዓመቱ እስከ ሶስት ሺህ ለሚደርሱ ፕሮጀክቶች የይሁንታ ፈቃድ እንደሚሰጡ ጠቁመው እስካሁንም ከ10ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ወደትግበራ ገብተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም አብራርተዋል።