የአፋርና አማራ ክልል ምክር ቤቶች በአዋሳኝ አካባቢዎች ግጭቶችን ለመከላከል በጋራ እየሰሩ እንደሆነ ተገለጸ

66

ወልዲያ መጋቢት 5/2011 አፋርና በአማራ ክልል ምክር ቤቶች  በአዋሳኝ አካባቢዎች  የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመከላከል  በጋራ እየሰሩ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

የሁለቱ ክልል ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ የውይይት መድረክ ዛሬ በወልዲያ ከተማ ተካሂዷል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅ ሰሙ ማሞ በመድረኩ እንዳሉት በሁለቱ ክልል ህዝቦች መካከል ዛሬ የተደረገው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የቀደመ አንድነታቸውን ይበልጥ ያጠናክራል።

የአፋርና አማራ  ህዝቦች በታሪክ፣ በኢኮኖሚ፣ በልማትና በሌሎችም  የረጅም ጊዜ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው አሁንም ግንኙነቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

በተለይ የሀገር ሽማግሌዎችና ሕዝቡ በጋራ ተባብረው ከሰሩ ከግጭት የፀዳ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት እንደሚቻል እምነታቸው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር  አቶ አወል አርባ በበኩላቸው ትምህርታቸውን የተማሩት በአማራ ክልል የተለያዩ ትምህርት ቤቶች መሆኑን ጠቅሰው ሁለቱም ህዝቦች  ቤተሰቦቻቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይ የአማራ ክልል በልማት ዘርፍ ለአፋር ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንና በቀጣይም በፊት የነበረው ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የአፋር ፍላጎት መሆኑን  አስረድተዋል፡፡

አፋር ከአማራ ክልል የጥቅም ብቻ ሳይሆን ከጥንት ጀምሮ የሁለቱ ህዝቦች የደም ትስስር ጭምር እንዳላቸውም  ጠቅሰዋል።

የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር  አቶ ገዱ አንዳርጋቸው  "የሁለቱ ክልል ህዝቦች የምክክር መድረክ ዓላማ ግንኙነታቸውን ማጠናከርና በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቀረት ነው" ብለዋል፡፡

ሁለቱም ሕዝቦች በኢትዮጵዊነት የማይደራደሩና ሰላም ወዳድ ሕዝቦች በመሆናቸው ከውይይቱ በኋላ የወሰን  አካባቢ አመራሮችና ሕዝቡ በየጊዜው እየተወያዩ ግጭቶችን እንዲያስወገዱ መልዕክታቸወን አስተላልፈዋል፡፡

ከሁለቱም ክልሎች አዋሳኝ ዞኖችና ወረዳዎች የመጡ ከ800 በላይ ተሳታፊዎች ባደረጉት ውይይትም ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርጉ ዕምነታቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከውይይት መድረኩ ተሰታፊዎች መካከል ከአፋር ክልል የመጡት ወይዘሮ ፋጡማ ኡመር በሰጡት አስተያየት ሁለቱ ሕዝቦች ተጋብተውና ተዋልደው መለያየት ከማይችሉበት ደረጃ የደረሱ መሆናቸወን ተናግረዋል፡፡

ከሁለቱም ክልሎች ከልብ የመነጨ የቀደመ ወዳጅነት መጠናከር ከቻለ ግጭቶች ተወግደው ዘላቂ ሰላም ሊመጣ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ከአማራ ክልል   የመጡት አቶ አሚ ሙሄ በበኩላቸው በሁለቱም  ህዝቦች መካከል የተደረገው የህዝብ ለህዝብ ውይይቱ  በወሰን አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ከሁለቱም ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የመጡ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች በሰጡት አስተያየት በሁለቱ ክልሎች መካከል ወንጀለኞችን አጋልጦ የመስጠት ችግር ስላለ ይህንን ስርዓት ማሲያዝ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የግጭት መንስኤዎች የመሬት ጥያቄና የግጦሽ እንዲሁም የንብረት ዘረፋ በመሆኑ አብዛኛውን ግጭት የሚያነሳሱት ሕዝቡ ሳይሆን አመራሮች መሆናቸውን አስተያየት ሰጭዎቹ ጠቅሰዋል፡፡

የጋራ ውይይቱ በወረዳና በቀበሌ ጭምር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሁለቱም ክልሎች የውይይቱ ተሳታፊዎች ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም