የሃዋሳ ከተማን ጸጥታ ለማስጠበቅ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ

105

ሃዋሳ መጋቢት 5/2011 የሃዋሳ ከተማን ጸጥታ ለማስጠበቅ በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን የደቡብ ክልልና የሃዋሳ ከተማ ፖሊስ አስታወቁ።

በከተማዋ ከፀጥታ ጋር የተያያዘ ስጋት ባለመኖሩ የመንግስት ሠራተኛውና ተቋማት ለሕብረተሰቡ መደበኛ አገልግሎታቸውን እንዲሰጡም ጥሪ ቀርቧል።

ከትናንት ጀምሮ በማህበራዊ ሚዲያ የተለቀቀ መረጃን ተከትሎ በሠራተኛውና በነዋሪው ላይ የተፈጠረውን ስጋት አስመልክቶ የደቡብ ክልልና የሃዋሳ ከተማ ፖሊስ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀልና ትራፊክ አደጋ መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ታዬ ጨርጋ እንደገለጹት ከትናንት ጀምሮ በማህበራዊ ሚዲያ በተለቀቀ መረጃ በሠራተኛውና በነዋሪው ላይ የጸጥታ ስጋት ተፈጥሯል፡፡

"ኃላፊነት ባልወሰዱ አካላት በተላለፈ ያልተገባ መልዕክት ሥራ መቆም የለበትም" ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ የክልሉ ፖሊስ ከፌደራል፣ ከመከላከያ፣ ከልዩ ኃይልና ከመደበኛ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት የከተማዋን ጸጥታ እያስጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሰላምን ለማጠናከርተገቢ ጥበቃ እየተደረገ በመሆኑ የመንግስት ሠራተኛውና ነዋሪዎች በሥራ ገበታቸው ላይ ተገኝተው መደበኛ አገልግሎት እንዲሰጡና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም  ወደሥራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ከፀጥታ ጋር የተያያዘ ምንም ስጋት አለመኖሩንም ምክትል ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል፡፡

የከተማውን ሰላማዊ ሀኔታ ማረጋገጥ የፖሊስ ብቻ ሳይሆን የዜጎችም ኃላፊነት በመሆኑ ሰራተኛውና ነዋሪዎች መደበኛ ሥራቸውን በመስራት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

"ሰላማዊና ዴሞክራሲዊ በሆነ መንገድ ተቃውሞን መግለጽ ይቻላል" ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ከዛ ውጭ የሚደረጉ ትንኮሳዎችና ዛቻዎችን መቆጣጠር የፖሊስ ኃላፊነት በመሆኑ ህዝቡ ከፀጥታ አካሉ ጋር እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡

የሃዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር መስፍን ዴቢሶ በበኩላቸው ከትናንት ጀምሮ የከተማውን ጸጥታ ለማስጠበቅ በቅንጅት እየተሰራና የእለት ግምገማም እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በከተማው ተዘግተው የነበሩ የንግድ ተቋማት ከትናንቱ በተሻለ ዛሬ መከፈታቸውን ገልጸዋል።

በከተማዋ ካሉ የባንክ ኃላፊዎች ጋርም በጉዳዩ ዙሪያ መነጋገራቸውን ነው የጠቆሙት፡፡

ባንኮችን ጨምሮ በመንግስትና በግል ተቋማት ላይ ያለውን ስጋት ለመቀነስ የፀጥታ ኃይሉ በበቂ ሁኔታ ጥበቃ እያደረገ መሆኑን ገልጸው በከተማውም እየተዘዋወረ ጥበቃውን የሚያጠናክረ ኃይል መኖሩን ተናግረዋል፡፡

መደበኛ አገልግሎት ከመስተጓጎል ውጪ የተፈጠረ ችግር አለመኖሩን ገልጸው የከተማው ነዋሪዎችም ሆኑ ሠራተኛው በቂ ጥበቃ መኖሩን ተገንዝበው ዕለታዊ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ህዝቡ በማህበራዊ ሚዲያ ለሚለቀቅ ያልተገባ መረጃ ትኩረት መስጠት እንደሌለበት የገለጹት ፖሊስ አዛዡ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችም ሠራተኛው ወደ ሥራ ገበታው እንዲመለስ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አመልክተዋል፡፡

ትምህርት ቤቶችና ወላጆች የትምህርት መቆራረጥ በተማሪው ውጤት ላይ የሚያመጣውን ተጽእኖ በመገንዘብ ከፖሊስ ጋር በቅንጅት እንዲሰሩም ጠይቀዋል፡፡

"በማህበራዊ ሚዲያ በሚተላለፉ ያልተገቡ መረጃዎች በሚወሰዱ እርምጃዎች ህብረተሰቡም መንግስትም ተጎጂ ናቸው" ያሉት ኮማንደር መስፍን ፖሊስ በሰላሙም በሁከቱም ከህዝብ ጋር እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም