በማዕከላዊ ጎንደር የዳስ መማሪያ ክፍሎችን ደረጃቸውን በጠበቁ ክፍሎች ለመቀየር እየተሰራ ነው

86

ጎንደር መጋቢት 5/2011 በማዕከላዊ ጎንደር አምስት ወረዳዎች የሚገኙ የመማሪያ ክፍሎች ደረጃቸውን በጠበቁ መማሪያ ክፍሎች ለመቀየር እንቅስቃሴ መጀመሩን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን እርካቤ ለኢትዮዽያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በዚህ ዓመት በክልሉ መንግስት በተመደበ ሁለት ሚሊዮን ብር 20 የዳስ የመማሪያ ክፍሎችን ደረጃውን በጠበቀ የመማሪያ ክፍሎች የመቀየር ስራ ተጀምሯል፡፡

የዳስ የመማሪያ ክፍሎቹ እንዲቀየሩ መደረጉ ተማሪዎች ለፀሐይ፣ ለአቧራና ለዝናብ ተጋልጠው ትምህርት ይከታተሉ የነበረበትን ሁኔታ የሚያስቀር መሆኑን አመልክተዋል።

የዳስ የመማሪያ ክፍሎቹ በምዕራብና ምሰራቅ በለሳ ኪንፋዝ አለፋና ጎንደር ዙሪያ ወረዳዎች የሚገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ መስፍን እንዳሉት ባለፈው ዓመት በኪንፋዝ አለፋ ወረዳ 80 የዳስ የመማሪያ ክፍሎች ደረጃውን በጠበቃ የመማሪያ ክፍል ተቀይረው በዚህ ዓመት ሥራ እንዲጀምሩ ተደርጓል።

በስድስት ትምህርት ቤቶች ስር የሚገኙት የዳስ የመማሪያ ክፍሎች እስከ 800 የሚደርሱ የቅድመና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች የሚማሩባቸው  ናቸው።

ላለፉት 20 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ከጭቃ የተሰሩ 80 የመማሪያ ክፍሎችን ከሕብረተሰቡ በሚሰባሰብ 3 ሚሊዮን ብር ወጪ በብሎኬት ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስረድተዋል።

ህብረተሰቡም የግንባታ ቁሳቁስ የሆኑ አሸዋና ድንጋይ ከማቅረብ ጀምሮ ጥሬ ገንዘብ በማዋጣት ለመማሪያ ክፍሎቹ ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እንደ አቶ መስፍን ገለጻ በምስራቅ በለሳ ኪንፋዝ ወረዳ በአምስት ትምህርት ቤቶች የሚገኙ 80 የዳስ የመማሪያ ክፍሎች ደረጃውን ወደ ጠበቀ የመማሪያ ክፍሎች ተቀይረው ዘንድሮ ሥራ እንዲጀምሩ ተደርጓል።

በኪንፋዝ ወረዳ የጭቅቂ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መላኩ ጫኔ ዕድሜአቸው ለትምህርት የደረሱ ታዳጊዎች ህጻናት በዳስ ውስጥ በድንጋይ ላይ ተቀምጠው እንደሚማሩ ተናግረዋል።

የዳስ ትምህርት ቤቶችን ደረጃቸውን በጠበቁ ትምህርት ቤቶች ለመቀየር የተጀመረው እንቅስቃሴ እንዳስደሰታቸው የተናገሩት አርሶ አደሩ ለመማሪ ክፍሎቹ የጉልበትና የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዚሁ ወረዳ ነዋሪና የተማሪ ወላጅ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ዘመድኩን አየለ ባለፈው ዓመት በመንግስት ድጋፍና በህዝቡ ትብብር የዳስ የመማሪያ ክፍሎች መቀየራቸው ለመማር ማስተማር ስራው ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

በተደረገው የትምህርት ንቅናቄ መርሃ ግብር ዘንድሮ ከ900 በላይ በሚሆኑ የዞኑ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 450 ሺህ ተማሪዎች ተመዝግበው በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም