አደጋው አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተቀባይነት አይጎዳውም

456

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011 በቅርቡ የደረሰው የአውሮፕላን አደጋ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተቀባይነት እንደማይጎዳው የአቪዬሽን ባለሙያዎች ተናገሩ።

ስጋቶችን መቀነስ እንጂ ማጥፋት ባለመቻሉ ከስጋትና ከአደጋ ነጻ የሆነ ኢንዱስትሪ የለም።

አስተማማኝ በሚባለው የአቪዬሽን ኢንዱስትሪም አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ችግሮች ከፍተኛ ዋጋ በማስከፈላቸው “የአቪዬሽን ደህንነት በደም ይጻፋል” ይባላል።

ከሰሞኑ ዓለም ያዘነበትና በኢትዮጵያ የተከሰተውም ይኸው ነው።

ከአዲስ አበባ ናይሮቢ ይበር የነበረ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ተከስክሶ 157 ሰዎች ህይወታቸውን አጡ።

የ35 አገራት ዜጎች ህይወታቸውን ያጡበት አደጋ እጅግ አሳዛኝና ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ ቢሆንም ሌላው ዓለም ለደህንነቱ ጥንቃቄ የወሰደበት ሆነ።

አምራቿን አገር አሜሪካ ጨምሮ ከ40 በላይ አገራት አየር መንገዶች ጉዳዩ እስኪጣራ ለጊዜው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላንን ሲያግዱ የአውሮፓ ህብረትም በአህጉሪቱ የአየር ክልል እንዳይበር ጭምር ከልክለዋል።

በዚህና አውሮፕላን ያዘዙ አየር መንገዶች ትእዛዛቸውን በመሰረዛቸው ቦይንግ ኩባንያ ትልቅ ጫናና አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በፊት ተመሳሳይ አደጋ የደረሰበት የኢንዶኔዥያ አውሮፕላን አንዱ የምርመራ ውጤት ቦይንግ በማክስ 8 አውሮፕላን ላይ ያደረገውን ማሻሻያ አብራሪዎች ሊረዱትና ጥንቃቄ ሊያደርጉበት በሚችል መንገድ በግልጽ በመመሪያ አለማካተቱ ነው።

ምንም እንኳን የኢትዮጵያው አደጋ የምርመራው ውጤት ገና ይፋ ባይሆንም “አዲስ ቴክኖሎጂ አዲስ ችግርና አዲስ መፍትሄ ይዞ ይመጣል” እንደሚባለው የተወሰዱ እርምጃዎች የሚያመላክቱት ቴክኖሎጂው ሊኖረበት የሚችለውን ክፍተት ነው።

የኤሮሪድ አቪዬሽን ሚዲያ ዋና ስራ አስፈጻሚና የግል አውሮፕላን አብራሪ ዮናታን መንክር ካሳ “ለእኛ ብቻ አይደለም ለዓለምም ጭምር ነው በዚህ አደጋ ላይ ህይወታቸውን የከፈሉት ውድ ዜጎች ለአለም አቪዬሽን ደህንነት አንድ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገው ነው ምክንያቱም ገና ምንም አይነት ኦፊሻል የሆነ ውጤት በሌለበት ሁኔታ አየር መንገዶች አላርምድ ሆነዋል፤ ተጠንቅቀዋል ራሳቸውን ፕሮቴክት አድርገዋል፤ ብዙ መንገደኞች ፕሮቴክት የሆኑበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል በሁለትና በሶስት ቀን ውስጥ”።

ከአደጋው በኋላ የዓለማችን ታዋቂ ሰዎች፣ የአቪዬሽን ባለሙያዎች፣ ስለ ኢትዮጵያ መልካም ተናግረው የማያውቁ የዓለም መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች ጭምር ስለ ኢትዮጵያ አየር መንገድ በጎ በጎውን ሲናገሩ ተደምጠዋል።

በተለይም የሲ ኤን ኤን ጋዜጠኛ ሪቻርድ ኩዌስት የኢትዮጵያ አየር መንገድ “በሌላ አገር አየር መንገድ ለመሄድ ፍርሃት ሲያድርባችሁ የሚመረጥ ነው” ማለት የሰጠው ምስክርነት የበርካቶችን ቀልብ ስቧል።

ዓለም ይህን ያህል በአየር መንገዱ እንዲተማመን የሆነው አንድ ደሃ አገር ሃብታም አገራት መመስረት ያልቻሉትን ብቁ አየር መንገድ መመስረት በመቻሏ ነው።

የኤሮሪድ አቪዬሽን ሚዲያ ዋና ስራ አስፈጻሚና የግል አውሮፕላን አብራሪ ዮናታን መንክር ካሳ″ለሆቴሎች አምስት ኮከብ የመጨረሻው እንደሆነ በአየር መንገድም አምስት ኮከብ አለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለ አራት ኮከብ ነው። በአፍሪካ ወስጥ አቻ የሌለው በቅርብ ርቀት እንኳን የሚወዳደረው አየር መንገድ የለም። በአውሮፕላን ቁጥር፣ በአውሮፕላን ቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል ብቃት፣ በሰው ኃይል አደረጃጀት፣ በትርፋማነት፣ በሚደርስባቸው መዳረሻዎች ብዛት፣ በሚያገኛቸው ዓለም አቀፍ ሽልማቶች በተለያዩ ዘርፎች በአንድ ዘርፍ አይደለም አየር መንገዱ የሚሸለመው በጣም በብዙ ዘርፎች ነው በየዓመቱ ሽልማት የሚወስደው እነዚህን ሁሉ መለኪያዎች በምናይበት ጊዜ አየር መንገዱ አፍሪካ ውስጥ ያለውን ውድድር አልፎ ከትልልቅ የአለም አየር መንገዶች ጋር ነው ራሱን እያወዳደረና እያተጋ ያለው”።

የአቢሲኒያ የበረራ ድርጅትና የአቪዬሽን አካዳሚ ኃላፊ ካፒቴን ሰለሞን ግዛው በበኩሉ “አየር መንገዱ ከዚህ በፊት የነበረው ታሪክ ይሄን ሁሉ ድጋፍ እንዲያገኝ አድርጎታል። ልማዱ ነው የሚባል አየር መንገድ አይደለም። ምክንያቱም ልምድ ያለው ነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ። አሁን ትናትና ተጠይቄ ነበር ካፒቴኑ ወጣት ነው ስምንት ሺህ ሰዓት ብቻ ነው ያለው የሚል እኔም የመለስኩት መልስ ስምንት ሺህ ሰዓት ያለው ሰው ብዙ ጊዜ ውጭ አገር ጡረታ የሚወጣበት ሰዓት ነው”።

በመሆኑም በቅርቡ የደረሰው አደጋ እጅግ አሳዛኝና ውዱን የሰው ልጆች ህይወት ያሳጣ ቢሆንም አየር መንገዱ የነበረውን መልካም ስምና ተቀባይነት የሚያሳጣው አይሆንም ይላሉ።

በአብራሪነት የካበተ ልምድ ያላቸው የአቢሲኒያ የበረራ ድርጅትና የአቪዬሽን አካዳሚ ኃላፊ ካፒቴን ሰለሞን ግዛው። “ከዓለም ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ስለአየር መንገዱ ጥራት ትናትና ሲያወዳድሩ ነበር፤ ከእንግሊዝ ከብሪቲሽ ኤርዌይስ ጋር፣ ከዩናይትድ ኤርላይንስ ጋር ከዴልታ እነዚህ እንግዲህ ዓለም ውስጥ ካሉት ትልልቆች ውስጥ የእነዛ የአውሮፕላኖቻቸው ዕድሜ ጠቅላላ አውሮፕላን ተወስዶ ዕድሜው አቬሬጅ ሲደረግ ዕድሜው 10 እና 2 ዓመት ነው። የኢትዮጵያ አየር መንንድ አራት አመት ተኩል ነው። እና በጣም ወጣት አውሮፕላኖችን ይዞ ጥሩ በጣም ለ70 ለ75 ዓመት አስደናቂ የሴፍቲ ሪከርድ ይዞ በዚህ አውሮፕላን አደጋ ያውም በኔ ግምት የእርሱ እጅ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ ነገር ተጠያቂ አይመስለኝም ስለዚህ የእርሱ ገበያ ይወድቃል ወይም ያንሳል ብዬ የማምንበት ምክንያት የለኝም”።

የኤሮሪድ አቪዬሽን ሚዲያ ዋና ስራ አስፈጻሚና የግል አውሮፕላን አብራሪ ዮናታን መንክር ካሳም እንዲሁ የምናዝነው ላጣናቸው ነፍሶች እንጂ አየር መንገዱስ የሚገጥመው ኪሳራ አይኖርም ባይ ናቸው።

አደጋ የደረሰበት አውሮፕላን ላይ መሳፈር የነበረባቸው ሰዎች በተለያየ ምክንያት ሲያመልጣቸው ከአደጋው በኋላም ጉዟቸውን በአየር መንገዱ ቀጣይ በረራ አድርገዋል።

እንደተባለውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ መደበኛ ስራውን እየሰራ ነው። ወጪ ገቢውም እንደተለመደው እንቅስቃሴ ላይ ነው።