የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የ5 ሺህ ሜትር ውድድር ከዳይመንድ ሊግ ውድደሮች መሰረዙን ተቃወመ

68

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011 የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የ5 ሺህ ሜትር ውድድር እ.አ.አ ከ2020 ጀምሮ ከሚካሄዱ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች መሰረዙን ተቃወመ።

የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ምክር ቤት መጋቢት 2 ቀን 2011 ዓ.ም በኳታር ርዕሰ መዲና ዶሃ ባደረገው ስብሰባ እ.አ.አ በ2020 ጀምሮ በሚካሄዱ የዳይመንድ ሊግ ውድድር የ5 ሺህ ሜትር ውድድር እንዲሰረዝ መወሰኑ የሚታወስ ነው።

ከ2020 ጀምሮ በዳይመንድ ሊግ የሚካሄደው ውድድር ከፍተኛው ርቀትም 3 ሺህ ሜትር ብቻ እንደሚሆንና በአጠቃላይ በወንድም በሴትም በተመሳሳይ 12 የውድድር አይነቶች ብቻ እንደሚኖሩ ምክር ቤቱ መግለጹም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የ5 ሺህ ሜትር ውድድር መሰረዙን ተከትሎ ተቃውሞውን ለዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፕሬዚዳንት ሴባስቲያን ኮ፣ ለአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን እና ለምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅን መግለጹን ፌዴሬሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ  ለዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፕሬዚዳንት ሴባስቲያን ኮ ዛሬ በጻፉት ደብዳቤ ውሳኔው በፌዴሬሽኑ ላይ ድንጋጤ እንደፈጠረና የማህበሩ አባል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ሀሳብን ያላከተተ እንደሆነ ገልጸዋል።

ማህበሩ ከውሳኔው በኋላ ባወጣው መግለጫ በጉዳዩ ዙሪያ ለአንድ ዓመት የቆየ ጊዜ ከአሰልጣኞች፣አትሌቶችና ከስፖርቱ ቤተሰቦችና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጋር ውይይት እንዳደረገ እንዲሁም ጥልቅ የሆነ ጥናት ማድረጉንም መግለጹን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በዓለም ደረጃ በ5 ሺህ ሜትር የሚወዳደሩ ተወዳዳሪዎች ውድድሩ በዳይመንድ ሊግ ቢኖር ምን ያህል ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው አሳማኝ ምክንያት እንዲያቀርቡ የሚያስችል የአንድ ቀን ውይይት መድረክ መዘጋጀቱንም ገልጾ እንደነበር አውስተዋል።

በውይይት መድረኮቹ ላይ የምስራቅ አፍሪካ አገራት የረጅም ርቀት ሯጮች እንዲሳተፉ የተመቻቸ እድል እንዳልነበረና ሀሳባቸውንም እንዳላቀረቡ ነው ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ ለማህበሩ ፕሬዚዳንት በጻፈችው ደብዳቤ የገለጸችው።

ከዚህ በፊት የ10 ሺህ ሜትር ውድድር ከዳይመንድ ሊግ መሰረዙን አስታውሰው አሁን 5 ሺህ ሜትር መሰረዙ እንደ ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት ጠንካራ ተወዳዳሪ ለሆኑ አገራት ፍትሐዊ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።

የ5 እና 10 ሺህ ሜትር ውድድሮች እንደ ኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች የሚቆጠሩና የእኛ የማንነት መገለጫ እንደሆኑም አመልክተዋል።

የሁለቱ ርቀት ውድድሮች በዳይመንድ ሊግ አለመኖራቸው ለዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮችና በአሎምፒክ ውድድር ለመሳተፍ የሚያስፈልገውን ሰዓት በተለይም በ10 ሺህ ሜትር ለማሟላት የሚያስፈልጉ ውድድሮችን ለማድረግ ይበልጥ ከባድ ፈተና እንደሚሆንም ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ውሳኔውን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ዳግም እንዲያጤነውና የማህበሩ ምክር ቤት የ5 ሺህ ሜትር ውድድር እ.አ.አ ከ2020 ጀምሮ ከሚካሄዱ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች እንዲሰረዝ የወሰነውን ውሳኔ ፌዴሬሽኑ ሙሉ ለሙሉ እንደማይስማማ ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ ለማህበሩ ፕሬዚዳንት ሴባስቲያን ኮ በጻፈችው ደብዳቤ ላይ አመልክታለች።

ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማህበሩም በጉዳዩ ዙሪያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ፈጣን ምላሽ እንደሚጠብቅም አክለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም