ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ያቀረቡትን መቃወሚያ ውድቅ አደረገ

135

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እነ ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኝው በተከሰሱበት የመርከብ ግዥ ላይ ያቀረቡትን መቃወሚያ ውድቅ አደረገ ።

የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ 12 ኃላፊዎችና ሁለት ግለሰቦች ከመርከቦች ግዥ ጋር በተገናኘ ከ544 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ጥር 6 ቀን 2011 ዓ.ም ክስ ተመስርቶባቸዋል።፡

በዚሁ የክስ መዝገብ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ ኮሎኔል በርሄ ወልደ ሚካኤል፣ ኮሎኔል ሙሉ ወልደ ገብርኤል፣ ብርጋዴር ጀኔራል ጠና ቁርንዲን ጨምሮ 12 ኃላፊዎችና ሁለት ግለሰቦች ይገኙበታል።

የፌዴራሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በነዚሁ ተከሳሾች ላይ ክስ የመሰረተው ዓባይና አብዮት በሚባሉት መርከቦች ግዥ ጋር በተያያዘ ነው፡፡

ተከሳሾቹ መርከቦቹን በ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ገዝተው በ7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ካሳደሱ በኋላ ወደ ሥራ ያስገቡዋቸው ቢሆንም፣ መርከቦቹ ትርፍ ሳይሆን ኪሳራ እንዳደረሱ በክሱ ተጠቅሷል፡፡

መርከቦቹ አዋጭ ባለመሆናቸውም በኪሳራ 607 ሺህ 432 ዶላር በመሸጣቸው፣ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ በአጠቃላይ የ544 ሚሊዮን 772 ሺህ 623 ብር ጉዳት መድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስታውቋል፡፡

ተከሳሾቹ በቀረበባቸው ክስ ላይ መቃወሚያቸውን ያቀረቡ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ያቀረበው ፍሬ ነገር በማስረጃ ማጣራት ሒደት የሚታዩ ናቸው ሲል ፍርድ ቤቱ መቃወሚያውን ውድቅ አድርጎታል።

ነገር ግን በክሱ መዝገብ ላይ ስልጣንን አለ አግባብ መጠቀምና  የመንግስትን ስራ በአግባቡ አለመምራት ተብሎ የቀረበው ክስ እንዲሻሻል ሲል ፍርድ ቤቱ ለመጋቢት 13 ቀን 2011 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም