የቆሼ መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራ ተጠናቀቀ

114

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011 በጃፓን መንግሥት የሚደገፈው የቆሼ መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራ መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገለጸ።

በመጋቢ 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የነበረው የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ ከ200 በላይ ሰዎች ለህልፈተ ህይወት ሲዳረጉ በርካቶች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ይታወሳል።

በቆሼ ያለው የቆሻሻ ክምር በድጋሚ ተደርምሶ ተመሳሳይ ችግር እንዳያስከትል የጃፓን መንግስት ፉኩካ የተሰኘ ዘዴን በመጠቀም በአካባቢው የሚከማቸውን ቆሻሻ ወደ ካርቦንዳይኦክሳይድ በመቀየርና በተፈጥሯዊ መንገድ እንዲበሰብስ የሚያደርገው ፕሮጀክት ሰኔ ወር 2010 ዓ.ም ይፋ ተደርጎ ነበር።

ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 100 ሺህ ዶላር ሲመድብ የጃፓን መንግሥት ደግሞ የሁለት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መልሶ ማቋቋም ደግሞ የቴክኒክ ድጋፍ አድርጓል።

በመሆኑም የፕሮጀክቱን የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራ መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ ዛሬ ጎብኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት መግለጫም የፕሮጀክት ግብ በቆሼ አካባቢ የደረሰው አደጋ ዳግም እንዳይከሰት የሚያስችለው የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ስራ መጠናቀቅ በአካባቢው ያለውን ስጋት እንደሚቀንስ ገልጸዋል።

በቆሼ ካለው 36 ሄክታር መሬት ውስጥ በመጀመሪያው ምዕራፍ የ1 ነጥብ 5 ሄክታር የቆሻሻ ክምር ፉኩካ የተሰኘ ዘዴ ወደ አፈርነት የተቀየረ ሲሆን ዕፅዋት የመትከል እና የመናፈሻ ስፍራ ማዘጋጀት ሥራዎች እንደሚቀሩ አብራርተዋል።

በቀጣይ አካባቢው መናፈሻ ስለሚሆን ለአካባቢው ነዋሪዎች ስጋት መሆኑ ቀርቶ ለኑሮ ተመራጭ እንደሚሆን ዶክተር ሰለሞን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ እሸቱ ለማ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ ጠቀሜታ የቆሻሻውን ክምር ወደ አፈርነት ከመቀየር ባሻገር በአካባቢ ጥበቃ እና በሰዎች ላይ የነበረውን ስጋት የሚያስወግድ እንደሆነም ተናግረዋል።

የአካባቢው ወጣቶች ፉኩካ የተሰኘውን ቴክኖሎጂ እንዲቀስሙ በፕሮጀክቱ ውስጥ ሲሰሩ እንደቆዩ የገለጹት አቶ እሸቱ ቀሪ ሥራዎችን በተገኘው እውቀት እና ልምድ ለማከናወን ዕቅድ እንዳለ ጠቁመዋል።

ከአዲስ አበባ ከተማ በቀን በአማካይ 3 ሺህ 200 ቶን ቆሻሻ ወደ ቆሼ የሚጣል ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከከተማዋ የሚወጣውን ቆሻሻ ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚሆነውን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ፍላጎት እንዳለ ጠቅሰዋል።

በቆሻሻ አሰባሰብ ላይ ተደራጅተው የሚሰሩ ወጣቶች በተያዘው በጀት ዓመት ቆሻሻን በመሸጥ 49 ሚሊዮን ብር ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

የቆሼ መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ በተያዘለት የጊዜ ገደብ መጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም