ለሴት ሥራ ፈጣሪዎች 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብድር መሰጠቱ ተጠቆመ

239

አዳማ  መጋቢት 5/2011 ለሴት ሥራ ፈጣሪዎች ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መሰራጨቱን የፌዴራል ከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ።

በኤጀንሲው የሴቶች ልማት ኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ፕሮጀክት ለባለድርሻ አካላት ያዘጋጀው የሦስት ቀናት የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ሰለሞን እንዳሉት የዓለም ባንክ በፕሮጀክቱ በኩል ባለፉት ዓመታት ከ2 ቢሊዮን 809 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር የሰጠው 11 ሺህ ለሚሆኑ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ነው፡፡

ከብድሩ ተጠቃሚዎች መካከል 733ቱ ሴቶች ከ500 ሺህ እስከ 2 ሚሊዮን ብር ብድር የወሰዱ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ በተመረጡ 12 የማይክሮፋይናስ ተቋማት አማካኝነት ብድሩ የተሰጠው በ10 ዋና ዋና ከተሞችና በ89 አነስተኛ አዋሳኝ ከተሞች በንግድ፣ በአገልግሎትና በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴት አንቀሳቃሾችን ሥራ ለማሳደግ ነው።

የገንዘብ ብድሩ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በሴቶች ባለቤትነት የሚንቀሳቀሱ ኢንተርፕራይዞች ገቢ እንዲያድግና የሚቀጥሩት የሰው ኃይል ቁጥርም እንዲጨምር የሚያግዝ መሆኑን አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ ሴቶች በሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ መሰረታዊ የንግድ ክህሎት፣ የሥራ ተነሳሽነትና የሙያ ስልጠና የተሰጣቸው ሲሆን በኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ እንዲሳተፉም እየተደረገ ነው።

ጥቅምት 2006 ዓ.ም የተጀመረው የሴቶች ልማት ኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ፕሮጀክት እስከ ታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ ታውቋል።

በእስካሁኑ የፕሮጀክቱ የትግበራ ሂደት ውጤታማ ሥራ በመሰራቱ የዓለም ባንክ እውቅና መስጠቱን ተከትሎ የአውሮፓ ሕብረትና የጣሊያን መንግስት 45 ሚሊዮን ዩሮ፣ የጃፓን መንግስት ደግሞ 50 ሚሊዮን ዶላር ብድር በቅርቡ ለመንግስት መስጠታቸውን አስታውሰዋል።

ገንዘቡን በተዘዋዋሪ ፈንድ ለመገልገል መንግስት መፍቀዱ ለፕሮጀክቱ ቀጣይነት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ሲሉም አስተባባሪው ገልጸዋል።

የፌዴራል ከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ መንግስቱ በበኩላቸው እንዳሉት ከዓለም ባንክ የተገኘው ብድር ሴት የሥራ ፈጣሪዎች እንዲነቃቁ የሚያበረታታ ነው።

“ከእዚህ በተጨማሪ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሴቶች ሰርተው ንብረት እንዲያፈሩና ለራሳቸው፣ ለማህበረሰብና ለቤተሰቦቻቸው መለወጥ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የሚያግዝ ነው” ብለዋል።

ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች መካከል በአዳማ ከተማዋ የምትኖረው ማርታ ከበደ በፕሮጀክቱ አማካኝነት ከወሳሳ ማይክሮፋይናንስ 250 ሺህ ብር ብድር ያለማሲያዣ በመውሰድ የልብስ ስፌት ስራዋን ማስፋፋቷን ተናገራለች።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ባደረገችው ጠንካራ እንቅስቃሴ የልብስ ስፌት ፍብሪካ፣ የፋሺን ዲዛይን ማሰልጠኛ ማዕከልና የጨርቃጨርቅ መሸጫ ሱቅ ባለቤት ለመሆን መብቃቷንና በእዚህም ከ20 ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሯን አመልክታለች።

“ብድር ከማግኘቴ በፊት ሰርቶ ለመንቀሳቀስ አዕምሮዬ ተገድቦ ነበር” የምትለው ማርታ ጠንክራ በመስራቷ በአሁኑ ወቅት ካፒታሏ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ማድረሷን ተናግራለች።