ወላይታ ድቻ አራት ተጨዋቾን በዝውውር አስፈረመ

81

ሶዶ መጋቢት 5/2011 አራት ተጨዋቾችን በዝውውር ማስፈረማቸውንና የዋና አሰልጣኝ ቅጥር መፈፀሙን የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ አስታወቀ።

ክለቡ በሁለተኛው አጋማሽ የፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን ቀድሞ የነበረውን ውጤታማነት ለመመለስ የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰዱን ገልጿል ።

የክለቡ ስራ አስኬያጅ አቶ አሰፋ ሆሲስ ለኢዜአ እንደገለፁት ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ መወዳደር ከጀመረ አንስቶ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ውጤት እየከዳው መጥቷል ።

የዘንድሮው የመጀመሪያው የፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን ከተጠናቀቀ በኋላ ላጋጠመው የውጤት ማሽቆልቆል ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት ወደ ቀድሞ ተወዳዳሪነቱ ለመመለስ የሚያስችሉትን የመፍትሄ እርምጃዎች መውሰድ ጀምሯል ።

" ከአሰልጣኙ ጋር የነበረ አለመግባባት፣ የተጨዋቾች የስነ-ምግባር ግድፈት፣ የአቋም መውረድና በሚፈለገው ልክ ዋጋ ያለመክፈል እንዲሁም የቡድን መንፈስ መጥፋት ለክለቡ ውጤት ማሽቆልቆል ምክንያቶች ተብለው ከተለዩ መካከል ተጠቃሽ ናቸው"ብለዋል ።

የክለቡ ቦርዱ ባስቀመጠው የመፍትሄ አቅጣጫ መሰረት ዋና አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃን እንዲሰናበቱ እንዲሁም ሁለት ተጫዋቾች ደግሞ በማስጠንቀቂያ እንዲታለፉ  መደረጉን ጠቅሰዋል።

ቡድኑን  የሚመጥን አሰልጣኝ ለማምጣት በተቀመጠ የውድድር መስፈርት መሰረት የቀድሞ የብሄራዊ ቡድንና አምና የኢትዮ ኤሌክትሪክ አሰልጣኝ የነበሩትን አሸናፊ በቀለን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ መቅጠሩን ተናግረዋል ።

የተሻለ ልምድና የኳስ ክህሎት ያላቸው ተጫዋቾችን በዝውውር ለማስፈረም በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ግብ ጠባቂ ጨምሮ አራት ተጨዋቾችን በዝውውር ለማምጣት ህጋዊ የውል ስምምነት ፊርማ መፈፀሙን ጠቁመዋል ።

በተከላካይ ስፍራ የቀድሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋች ደጉ ደበበን ለቀሪው የውድድር ወራትና ከወላይታ ሶዶ ከነማ  አንተነህ ጉግሳን ለ16 ወራት ክለቡ ማስፈረሙን ተናግረዋል።

በአጥቂ ስፍራ ከሃዋሳ ከነማ ተቀንሶ ያለክለብ የተቀመጠውንና የቀድሞ የክለቡን ተጫዋች አላዛር ፋሲካን ለቀሪው ስድስት ወራት እንዲሁም የቀድሞ የብሄራዊ ቡድንና የወልዲያ እግር ኳስ ቡድን ግብ ጠባቂ  የነበረውን ደረጀ ዓለሙን በተመሳሳይ ለስድስት ወራት ማስፈረሙን ገልጸዋል፡፡

" የቀድሞ የክለቡ የመሃል ክፍል ተጨዋችና ልዩነት ፈጣሪ የነበረውን በዛብህ መለዮን ከፋሲል ከነማ በውሰት ውል ለማስፈረም ውይይቶች እየተደረገ ነው"ብለዋል።

የዝውውር ሂደታቸውን አጠናቅቀው ከክለቡ ጋር ስራቸውን ለጀመሩ ተጨዋቾች  በየወሩ ከ250 ሺህ ብር በላይ ለደመወዝ ወጪ እንደሚያደርግ አመላክተዋል።

በሌላ በኩል ክለቡ ላጋጠመው የውጤት ማሽቆልቆል ምክንያት ተብለው ለተለዩ ውጫዊ ጉዳዮችም የመፍትሄ አቅጣጫ ተቀምጦ አፋጣኝ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል ።

በእርምጃው መሰረት በሜዳ ላይ የሚስተዋሉ የዲሲፕሊን ግድፈቶችን ለማስተካከል የተሻለ የደጋፊ ማህበር አደረጃጀት እንዲፈጠር መደረጉን  ጠቅሰዋል ።

የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ በቀጣይ እሁድ ከስሁል ሽሬ ጋር የፕሪሚየር ሊጉን የሁለተኛ የውድድር ዓመት የመክፈቻ ጨዋታ በሜዳው እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያወጣው የውድድር መርሃ ግብር ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም