የጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርመራና ህክምና በሁሉም ጤና ጣቢያዎች እንዲሰጥ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

88

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011 ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አስፈላጊ ምርምራና በቂ ህክምና በሁሉም ጤና ጣቢያዎች እንዲደርስ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ህብረተሰቡም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመከላከል ጥረት እንዲያደርግ ተጠይቋል።

ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ የኩላሊት ህመም ማህበር ጋር በመተባበር የአለም የኩላሊት ቀንን ነጻ የኩላሊት ፣ የደም ግፊትና የስኳር ምርምራ በማድረግና የግንዛቤ ማስጨበጫ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በማካሄድ አክብሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በሚኒስቴሩ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ቡድን መሪ ዶክትር ሶስና ኃይለማሪያም እንደገለጹት፤ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በአሁኑ ወቅት አሳሳቢና ጎጂ እየሆኑ መጥተዋል።

በተለይም ስኳር፣ ደም ግፊት፣ ልብ፣ ኩላሊትና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ ሽታዎችን ከጤና እክል ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እንደሚያስከትሉም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የተላላፊ በሽታ ህክምና በበቂ መጠን ተደራሽ እንዲሆን ለማስቻል ከአጋር ድርጅቶችና ከሙያ ማህበራት ጋር በመሆን በሁሉም ጤና ጣቢያዎች እንዲሰጥ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ ራሱን ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ለመከላከል መንቀሳቀስ እንዳለበትም ዶክተር ሶስና ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የኩላሊት ህመም ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ቴዎድሮስ አጎናፍር በበኩላቸው፤ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የህክምና ወጪ ከፍተኛ ነው።

በተለይም የኩላሊት በሽታ ህክምና ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ በኢትዮጵያ ላሉ ታካሚዎች በበቂ ሁኔታ ለማድረስ አስቸጋሪና የአገርንም ኢኮኖሚ የሚፈታተን እንደሆነ ጠቁመዋል።

ይህንንም አስቀድሞ ለመከላከል ህብረተሰቡ ራሱን ከበሽታው እንዲጠብቅና ግንዛቤ እንዲኖረው መሰራት እንዳለበትም ተናግረዋል።

በአለም ላይ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት በየአመቱ 41 ሚሊዮን ሰዎች ህይወታቸውን እንደሚያጡ የአለም የጤና ድርጅት የ2018 ሪፖርት ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም