በሸማቾች መብት ጥበቃ ላይ የሚሰሩ የሲቪከ ማህበራትን ማቋቋም ያስፈልጋል

195

አዲስ አበባ መጋበት 5/2011 ሸማቾች በግብይት ወቅት የሚያጋጥማቸውን ፍትሃዊ ያልሆነ ዋጋ ለመቆጣጠር በሸማቾች መብት ጥበቃ ላይ የሚሰሩ የሲቪከ ማህበራትን ማቋቋም እንደሚያስፈልግ አንድ የህግ ባለሙያ ገለጹ።  

የንግድ ውድድርና ሸማቾች መብት ጥበቃ ባለስልጣን ”የሸማቾች መብት ጥበቃ ሲቪክ ማህበራት አደረጃጀት ነባራዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ በተደራጀ አኳሃን የሸማቹን መብትና ጥቅምን ከማስጠበቅ አንጻር” በሚል ርዕስ የሁለት ቀናት ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።  

በውይይት መድረኩ በሸማቾች መብቶች ጥበቃ ላይ ያተኮረ ገለጻ ያደረጉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት ዶክተር መሰንበት አሰፋ እንዳሉት፤ ሸማቾች በንግድ ግብይት ወቅት በርካታ ችግሮች ይገጥሟቸዋል።

ፍትሃዊ ያልሆነ ዋጋ፣ ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ባዕድ ነገሮችን ከምግብ ጋር መቀላቀል፣ የጥራት መጓደልና ሌሎች ችግሮች ሸማቹን ከሚያጋጥሙት መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሸማቾችና የንግዱ ማህበረሰብ በሸማቾች መብትና ጥበቃ ዙሪያ ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ ችግሮቹን ለመፍታት ሲቸገሩ ይስተዋላል። 

በተደራጀ መልኩ በሸማቾች መብትና ጥበቃ ላይ የሚሰሩ ከመንግስት ነጻ የሆኑ ጠንካራ ሲቪክ ማህበራት ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ዶክተር መሰንበት ጠቁመዋል።

እንደ ዶክተር መሰንበት ማብራሪያ የሲቪክ ማህበራት ለመብቱ ተሟጓች የሆነ ሸማች ማህበረሰብ ለመፍጠር፣ በምርቶች ጥራትና ደህንነት ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር ለማጠናከር በሸማቾች መብትና ደህንነት ላይ የሚሰሩ ተቋማት የጎላ ሚና አላቸው።

በኢትዮጵያ የሲቪክ ማህበራት አደረጃጃት ላይ ያለው የህግ ማዕቀፍ የተሻሻለ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የሸማች ሲቪክ ማህበራትን ለማቋቋም የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመዋል።

በትምህርት ስርዓቱ ላይ የሸማቾችን መብት ላይ ያተኮሩ ትምህርቶችን ማካተት፣ የገበያ ስርዓቱን ማዘመን፣ ከሸማቾች ጤናና ደህንነት አኳያ ቅድሚያ ሊሰጣቸው በሚገባቸው ምርቶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደ ምክረ ሀሳብ ያቀረቧቸው ነጥቦች ናቸው። 

የንግድ ውድድርና የሸማቾች መብት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል ተክሉ በበኩላቸው በመንግስት ተቋማት ግንዛቤ የመፍጠርና የህግ ማስፈጸም ተግባራት ቢከናወኑም የሸማቾችን መብቶችንና ጥቅሞች በሚፈለገው ደረጃ ለማስጠበቅ የተደራጁ የሲቪክ ማህበራት ሚና ጉልህ እንደሆነ አብራርተዋል።

የሌሎች አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተሞክሮ እንደሚያሳየው የሸማቾች መብቶች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች የሚከናወኑት በመንግስት ተቋማት ብቻ ሳይሆን ነጻ በሆኑ የሸማቾች መብት ጥበቃ ሲቪክ ማህበራት ጭምር እንደሆነም አቶ ሚካኤል አስረድተዋል። 

ማህበራቱ ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር የሸማቾችን ደህንነት ሊጎዱ የሚችሉ ምርቶችንና አገልግሎቶች በሚያቀርቡ የንግድ ድርጅቶች ላይ ጫና በመፍጠር ሸማቾችን ወክለው በህግ እስከ መጠየቅ የሚደርስ ሚና እንደሚጫወቱም ጠቁመዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ጠንካራ የሸማቾች መብት ጥበቃ ማህበራት በሚገኙባቸው አገሮች የንግድ ድርጅቶች የሸማቾችን መብት የመጣስ ዕድላቸው ዝቀተኛ ነው።

የንግድ ውድድርና የሸማቾች መብት ጥበቃ ባለስልጣን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የሸማቾች ሲቪክ ማህበራት የሚቋቋሙበትንና የሚጠናከሩበትን ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር እንደሚሰራም አመልክተዋል።