ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው የተከሰሱበትን የትራክተር ግዥ ወንጀልን እንዳልፈፀሙ ገለጹ

122

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011 ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው በተከሰሱበት የትራክተር ግዥ ወንጀልን እንዳልፈፀሙ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ገለጹ።

የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢነጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ በመንግሥት ላይ ከ319 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ተከሳሾች ዛሬ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ሥልጣናቸውን ያለአግባብ ተጠቅመው በመንግሥት ሃብት ላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ የቀድሞ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ፣ አምስት ኃላፊዎችና ሦስት በግል ሥራ የተሰማሩ ግለሰቦች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል።

በዚህ የክስ መዝገብ ውስጥ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁሩንዲ፣ ኮሎኔል ደሴ ዘለቀ፣ ኮሎኔል ጌትነት ጉድያ /ያልተያዙ/፣ ኮሎኔል ጎይቶም ከበደ/ያልተያዙ/፣ አቶ ቸርነት ዳና፣ ወይዘሮ እሌኒ ብርሃን /ያልተያዙ/ እና አቶ ረመዳን ሙሳ ይገኙበታል።

ተከሳሾቹ በዋናነት የቀረበባቸው ክስ ለአዳማ እርሻ መሣሪያዎች ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ አገልግሎት ከሚውሉ ትራክተሮች ግዥ ጋር የተገናኘ መሆኑን ዐቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል።

ተከሳሾቹ በጥቅም በመመሳጠር ማንኛውም ግዥ በግልጽ ጨረታ መፈጸም እንዳለበት መደንገጉን እያወቁ፣ መመርያውን በመተላለፍና በርካታ ትራክተሮች ያለጨረታ እንዲገዙ ማድረጋቸውን ዐቃቤ ሕግ በመሠረተባቸው ሰባት ክሶች ውስጥ በዝርዝር አስቀምጧል።

በዚሁ የክስ መዝገብ ውስጥ 1ኛ ተከሳሽ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ በኃላፊነት የሚመሩት ተቋም ከተጣለበት ተልዕኮ አንፃር ማንኛውንም ግዥ በሕጉና በመመሪያው መሠረት መከናወኑን፣ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት የሆነው የውጭ ምንዛሪ ለተገቢው ዓላማ መዋሉን የማረጋገጥና የመቆጣጠር ኃላፊነት ቢኖርባቸውም ሃላፊነታቸውን እንዳልተወጡ በክሱ ተገልጿል፡፡

ነገር ግን ከዚህ  በተፃራሪ ሁኔታ ከሕጋዊ የግዥ ሥርዓት ውጪ ለሙስና ምቹ የሆነ ሕገወጥ የግዥ ሥርዓት በመዘርጋት ግዥና ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

ሜቴክ በዕቅድና ጥናት ላይ የተመሠረተ የግዥ ፍላጎት ከኢንዱስትሪው ሳይቀርብ፣ ስለሚገዙት የትራክተር ዓይነቶችና ተገቢ ዝርዝር ሁኔታ ሳይዘጋጅ፣ ትራክተሮቹ በተጠቃሚ ዘንድ ተፈላጊና የመግዛት አቅምን ያገናዘቡ መሆናቸው ሳይረጋገጥ፣ የጥራትና የዋጋው ሁኔታ በኢንዱስትሪው ባለሙያዎች ጥናት ሳይካሄድና ቀደም ብሎ የተገዙ ትራክተሮች ባልተሸጡበት ሁኔታ የሚገኘውን ሕገወጥ ጥቅም ብቻ በማሰብ፣ ከደላሎችና ከጉዳይ አስፈጻሚዎች ጋር በመመሳጠር ግዥው መፈጸሙን የዐቃቤ ሕግ ክስ አብራርቷል፡፡

በዛሬው እለትም ሜጀር ጀነራል ክንፈ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ጠና፣ አቶ ቸርነት ዳና እና አቶ ረመዳን ሙሳ በአቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ወንጀል አለመፈፀማቸውን ፍርድ ቤቱ የእምነት ክሕደት ቃላቸውን በተቀበላቸው ወቅት በዐቃቤ ህግ የቀረበባቸውን የወንጀል ክስ እንዳልፈጸሙ ገልፀዋል።

አቃቤ ሕግም በበኩሉ ተከሳሾቹ ለፍርድ ቤቱ የሰጡት የክሕደት ቃል በመሆኑ አሉኝ የሚላቸው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች እንዲቀርቡለት ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ሕግን ምስክሮች ቃል ለመስማት ለግንቦት 1 ቀን 2011ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

በተጨማሪም በዚሁ መዝገብ ተከሰው በቁጥጥር ስር ያልዋሉ 4ኛ፣ 5ኛና 7ኛ ተከሳሾች በጋዜጣ ተጠርተው ሊመጡ ባለመቻላቸው ጉዳያቸው በሌሎበት እንዲታይ ተወስኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም