በባህርዳር ከተማ የሚገኘው የእጅ ኳስ ሜዳ ለውድድር ዝግጁ ሆነ

384

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011 በባህርዳር የሚገኘው የእጅ ኳስ ሜዳ የፕላስቲክ ንጣፍ ስራ ተጠናቆ ለውድድር ዝግጁ ሆኗል።

የአሜሪካው የስፖርት ሜዳ ንጣፎች (sports surfacing) ኩባንያ ኮኖር ስፖርት ስራውን በማጠናቀቁ ሜዳው ትናንት በይፋ ተመርቆ የርክክብ ስነ ስርአት ተካሂዷል።

በስነ ስርአቱ የክልሉ የስፖርት ኮሚሽን ሜዳውን የተረከበ ሲሆን በእለቱ የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳ፣ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ፍትህ ወልደሰንበት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የፌዴራልና የአማራ ክልል የስፖርት ኮሚሽኖች ሁለት ሚሊዮን ብር፣ የዓለም አቀፉ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን 30 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ለንጣፉ የፋይናንስ ድጋፍ አድርገዋል።

ሜዳው ከዚህ በፊት ተጫዋቾችን ለጉዳት ይዳርግ እንደነበር አስታውሰው አሁን የተሰራው ዘመናዊ የፕላስቲክ ንጣፍ ለተጫዋቾች ምቹና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንደሆነም አመልክተዋል።

የፕላስቲክ ንጣፉ 15 ዓመት ዋስትና እንዳለውና  ስራውን ያከናወነው ኮኖር ስፖርት ሜዳው ቢበላሽ ለተጠቀሱት ዓመታት እድሳትና ጥገና እንደሚያደርግ ነው አቶ ሞላ ያስረዱት።

ሜዳው በዘመናዊ መልክ መዘጋጀቱ በክልሉ ስፖርቱ እንዲስፋፋና የክለቦችን ቁጥር ለማሳደግ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በቀጣይም በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ የእጅ ኳስ ሜዳዎችን የማስፋፋት ስራ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ስፖርት በ1960 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲ መምህራን አማካይነት ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ ይነገራል። ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላም የእጅ ኳስ ጨዋታ በአራት ክለቦች የመጀመርያ ጨዋታ እንደተደረገ መረጃዎች ያስረዳሉ።

በ1962 ዓ.ም የኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን ተመስርቶ አሥር ክለቦች ተደራጅተው አራት ኪሎ ወወክማ በተካሄደ ውድድር መካፈል ችለዋል።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የዓለም አቀፍ አባልነት ካገኘ በኋላ ሴት ተጫዋቾችን በማካተት ውድድር ሲያካሂድ ቆይቶ ፌዴራል ፖሊስ፣ ጉምሩክና ኦሜድላ የመሳሰሉ ክለቦች በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።