የሴቶች ጉዳይ የኛም ጉዳይ ነው-የወንዶች አጋርነት

151

አዲስአበባ መጋቢት 5/2011 በዓይነቱ ለየት ያለና የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ በወንዶች አጋርነት የሴቶች ቀን በዓል (ማርች 8) ዛሬ "እኛ ያላንቺ" በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ ተከበረ።

በበዓሉም ይኸው የወንዶች አጋርነት "የሴቶች ጉዳይ የሰብዓዊነትና የህልውና ጉዳያችን ነው" ሲል  ሴቶች ላይ የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ ውይይት አድርጓል።

በውይይቱም ሴቶች እስካሁን በሚፈለገው ደረጃ ተሳታፊና ተጠቃሚ አለመሆናቸው ተገልጾ የተለያዩ ጥቃቶችን የሚያደርሱ አካላትን የማጋለጥ ስራ ላይም ሪፖርት የሚደረገው 20 በመቶው ብቻ እንደሆነ ነው የተነገረው።

የአጋርነቱ ተሳታፊ አቶ አቶ መለሰ ድንቁ እንደተናገሩትም ወንዶች ሴቶች ላይ ማንኛውንም አይነት በደልና ግፍ እንዳያደርሱ መከላከል ሰብዓዊነት ነው።

ይህንን ጥቃት ሲያደርስ የታዩትን አካላትንም ለህግ አካላት ማመልከት እንደሚገባቸው ተናግረው፤  የሴቶች ጉዳይ ላይ የተዛባ አመለካከት ላላቸውም ትምህርት መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። 

የሴቶችን ጥቃት መቀነስን መሰረት ያደረጉ የህብረተሰብ ግንዛቤ የማጎልበት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለፀው የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ በአስሩ ክፍለ ከተማዎችና በ117ቱ ወረዳዎች ጥቃት ተከላካይ ኮሚቴ አቋቆሞ በመስራት ላይ መሆኑን ነው የገለጸው።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ አብረሃ እንዳሉት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ከመከላከል ጎን ለጎን የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ከማሳደግ አኳያ ሴቶችን በህብረት ስራ ማህበራት በማደራጀት ጊዜና ጉልበት ቆጣቢ ለሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግም እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዓሉ በተለያዩ ጊዜያት አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች መታሰቢያ እንደሆነም ነው የተገለጸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም