ህብረተሰቡ ዳግም በመነቃቃት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

63

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011ህብረተሰቡ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ያለውን አዎንታዊ ተሳትፎና ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ግድቡን በኢትዮጵያ መንግስትና በህብረተሰቡ ሙሉ ተሳትፎ ለመገንባት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግንባታው 65 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።

ለግድቡ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት እለት አንስቶም የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሁሉም አቅጣጫ የድጋፍ ሠልፎችን በማካሄድ ደግፈዋል፤ ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ከተማሪ እስከ ምሁሩ ድረስ በእውቀት፣ በገንዘብና በጉልበት ለመርዳት ቃል ገብተው ተንቀሳቅሰዋል።

ይኸው በወቅቱ በነበረው የዋጋ ተመን “በ80 ቢሊዮን ብር ወጪ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል” በሚል እምነት የተጀመረው የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫው ግድብ ግንባታ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ መጠናቀቅ ባለመቻሉ በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ ፈጥሮ ቆይቷል።

በታቀደለት ጊዜ አለመከናወኑን ተከትሎም ህብረተሰቡ ድጋፉን ቀንሶ እንደነበር የሚናገሩት የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቀርተ ታምር ናቸው።

ወይዘሮ ፍቀርተ ከኢዜአ ሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደሚናገሩት የግንባታ ሂደቱ ችግሮች እንዳጋጠሙት በተገለጸበት ወቅት የህብረተሰቡ የድጋፍ ተሳትፎ ለማወቅ በተካሄደው የዳሰሳ ጥናት 50 በመቶ ያህሉ ነበር ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ መግለጻቸውን ያሳወቁት።

የተቀሩት ግን ግንባታው በመንግስት ወጪ እንዲካሄድ ሀሳብ ማቅረባቸውን ይገልጻሉ።

አሁን ግን በተከናወኑ የተግባቦት ስራዎች የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ማንሰራራቱን ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ያመለከቱት። 

በሳሊኒ ኮንስትራክሽን የሚገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም የሚኖረው ሲሆን፤ ለዚህ ትልቅ ፕሮጀክት ህብረተሰቡ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ወደ 484 ሚሊዮን ብር ቦንድ መግዛቱ በግንባታው ላይ እምነት እንዳለው እንደሚያሳይ ነው ከምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ መረዳት የሚቻለው።

እንደወይዘሮ ፍቅርተ ገለጻ፤ በፕሮጀክቱ ግንባታ በኩል ያጋጠሙ እክሎች ተለይተውና መንግስት በጀት መድቦ አሁን በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተሰራ ነው።

በቀጣይም በተቀመጠው ስትራቴጂ ተከታታይነትና ግልጽነት ያለው መረጃ ለህብረተሰቡ በማድረስ የተጠናከረ ስር እንደሚሰራ ነው ያመለከቱት።

ህዝብ ለግድቡ ግንባታ ላበረከተው የላቀ አስተዋጽኦም የታላቁ ህዳሴ ዋንጫ ከስድስት ዓመት በፊት የተበረከተ ሲሆን፤ በየክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ዞሮ ቅስቀሳና የገቢ ማሰባሰቢያ እንዲሆን በተደረገ እንቅስቃሴ ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱ ተገልጿል።

ዘንድሮም የግድቡ የስምንተኛ ዓመት በዓል ሲከበርም በአገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ ባጋጠሙት ችግሮችና የወደፊት አቅጣጫ ላይ በሰፊው ውይይት እንደሚካሂድ ተገልጿል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሩጫ፣ የቦንድ ሽያጭ ሳምንት፣ የችቦ መቀባበል ሥነ ሥርዓት፣ የዓባይ ቀን የሥነ ጽሑፍ ምሽት፣ የእግር ኳስ ውድድር፣ የዓባይ ቀን የጎዳና ላይ ትርዒት፣ የብስክሌት ውድድር፣ የሕፃናት የሥዕል ውድድር፣ የሥዕልና የፎቶ ግራፍ ዓውደ ርዕይና ሌሎች መርሃ ግብሮች እየተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል።

ህብረተሰቡም በነዚህ መርሃ ግብሮች ላይ በመሳተፍ "ታላቁን ፕሮጀክታችንን ከዳር እናድርስ" በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም