የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች የፊታችን ቅዳሜና እሁድ ይካሄዳሉ

229

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች የፊታችን ቅዳሜና እሁድ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ።

ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከጎንደር ከተማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

እሁድ መጋቢት 8 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ፌደራል ፖሊስ ከመከላከያ ፤ ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከቡታጅራ ከተማ በተመሳሳይ ከጠዋቱ ሶስት  ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በዘጠነኛው ሳምንት መርሃ ግብር ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችና ከምባታ ዱራሜ አራፊ ክለቦች ናቸው።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ14 ነጥብ ሲመራ፣ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ13 ነጥብ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ11 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

እስካሁን በፕሪሚየር ሊጉ ምንም ጨዋታ ያላሸነፈው ድሬዳዋ ከተማ ያለ ምንም ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ከነገ ጀምሮ በምድብ አንድና ሁለት በሚደረጉ ጨዋታዎች ቀጥሎ ይካሄዳል።

ነገ በምድብ አንድ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ከቢጂአይ ኢትዮጵያ፣ ከነገ በስቲያ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ከወልቂጤ ከተማ እና እሁድ መጋቢት 8 ቀን 2011 ዓ.ም ቢጂአይ ኢትዮጵያ ከወልቂጤ ከተማ ባህርዳር ላይ በተመሳሳይ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በምድብ ሁለት ነገ ሀዋሳ ከተማ ከጎንደር ከተማ፣ ከነገ በስቲያ ሀዋሳ ከተማ ከፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እና እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጎንደር ከተማ ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሀዋሳ ላይ በተመሳሳይ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

በኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን አዲስ የውድድር ፎርማት መሰረት በሴቶች በምድብ አንድና ሁለት ያሉ ክለቦች በቅደም ተከተል ወደ ባህርዳርና ሀዋሳ በማቅናት ለሶስት ተከታታይ ቀናት እርስ በርስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በሁለቱም ጾታዎች በተመሳሳይ ስድስት ክለቦች እየተሳተፉ ይገኛሉ።