የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር የፊታችን ቅዳሜና እሁድ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራል

138

አዲስ አበባ መጋቢት5/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ውድድር የፊታችን ቅዳሜና እሁድ በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራል።

ውድድሩ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ይጀመራል ቢባልም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መርሃ ግብሩ ላይ ማስተካካያ ማድረግ በማስፈለጉ በአንድ ሳምንት እንዲራዝም እንዳደረገው የሚታወስ ነው።

በዚሁ መሰረት የሊጉ 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት የሚካሄዱ ይሆናል።

በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ ከሀዋሳ ከተማ ከነገ በስቲያ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት የሚያደርጉት ጨዋታ የፕሪሚየር ሊጉ የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ነው።

እሁድ መጋቢት 8 ቀን 2011 ዓ.ም በፕሪሚየር ሊጉ ሰባት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በአዲስ አበባ ስታዲየም መከላከያ ከደቡብ ፖሊስ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

በክልል ከተሞች በመቐለ ደደቢት ከሊጉ መሪ መቐለ ሰብዓ እንደርታ፣ በባህርዳር ባህርዳር ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በጎንደር ፋሲል ከተማ ከሲዳማ ቡና።

እንዲሁም በጅማ  ጅማ አባ ጅፋር ከአዳማ ከተማ፣ በሶዶ  ወላይታ ድቻ ከስሑል ሽረና በድሬዳዋ ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ35 ነጥብ ሲመራ፣ ሲዳማ ቡና በ30 ነጥብ 2ኛ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ26 ነጥብ 3ኛ ደረጃን ይዘዋል።

ደቡብ ፖሊስ፣ ስሑል ሽረና ደደቢት በቅደም ተከተል ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙና የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤል በተመሳሳይ 11 ግቦች ሲመሩ የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በ10 ግቦች ይከተላል።

የፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር መርሃ ግብር መጋቢት 7 ቀን 2011 ዓ.ም ተጀምሮ ሰኔ 9 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።