ከማንኛውም እንቅስቃሴ በፊት ህዝባዊ ሰላምን ማስቀደም ይኖርብናል-ፖለቲካ ፓርቲዎች

109

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011 ከማንኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፊት ህዝባዊ ሰላምንና የህግ የበላይነትን ማስከበር ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ።

የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ አሰራር የቃል ኪዳን ሰነድ ፊርማ ስነ ስርዓት በሄልተን ሆቴል እየተካሄደ ነው።

ፓርቲዎች በሰነዱ ላይ ፊርማቸውን እያስቀመጡ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም በሂልተን ሆቴል ተገኝተው ገዥውን ፓርቲ ኢህአዴግ ወክለው ፊርማቸውን አስቀምጠዋል።

ፓርቲዎቹ ዛሬ በፊርማቸው የሚያፀድቁትን የቃል ኪዳን ሰነድ አስመልክተው ንግግር በማድረግ ላይ ሲሆኑ ቀጣዩን ምርጫ እውን ለማድረግ መጀመሪያ ሰላምን፣ የህግ የበላይነትን ማስከበርና ማክበር ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።

ፓርቲዎቹ "ሰላም ሳይኖር እውነተኛ ምርጫ፣እውነተኛ ምርጫ ሳይኖር ጠንካራ ዴሞክራሲ፣ዴሞክራሲ በሌለበት ደግሞ ሃገርንም መምራት ያስቸግራል" ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም ሁሉም ፓርቲ ከልዩነት ይልቅ አንድ በሚያደርጓቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ከለውጥ በኋላ ያለውን እድል ተጠቅሞ ለህዝብ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለፍትህና ለሰላም ካልሰሩ ውጤቱ አደገኛ ነው ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

ፓርቲዎቹ ይህን ቃል ኪዳን መፈራረማቸው ፓርቲዎቹን አንድ በሚያደርጓቸው ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚያስችላቸውና ሁሉም ፓርቲ ሰነዱን ተግባራዊ ካደረገና ከአባላቱና ከሀዝቡ ጋር ከሰሩ ትልቅ ውጤት እንደሚያመጣም በመድረኩ ላይ ተደጋግመው የተነሱ ነጥቦች ናቸው።

ይህ ቃል ኪዳን በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚኖርን ግንኙነት እንዲሁም በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሰራር ስርአት የቃል ኪዳን ሰነድ ሲሆን ፓርቲዎቹ በተደጋጋሚ ሲያደርጓቸው በነበሩ ውይይቶች ናቸው ለመፈራረም የተስማሙት።

የቃል ኪዳን ሰነዱ 20 አንቀፆች እንደሚኖሩትም ተገልጿል።

በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች እና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ግንኙነት መልካም ለማድረግ ታስቦ የቃል ኪዳን ሰነዱ እንደተዘጋጀ ነው የተገለፀው።

በ1ኛውና በ2ኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብሰባ ወቅት ሊሻሻሉ ይገባቸዋል ተብለው የተነሱ ሃሳቦች ተስተካክለው ነው የቃል ኪዳን ሰነዱ ከዚህ ቀደም ለመፈራረም የተስማሙት።

አሁን ደግሞ ቃል የገቡትንና ያፀደቁትን የቃል ኪዳን ሰነድ በፊርማቸው ለማረጋገጥ ነው  የፖለቲካ ፓርቲዎች ሂልተን ሆቴል ላይ የተሰባሰቡት።

ዛሬ በሂልተን ተገኝተው ከተሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች 66ቱ እውቅና የተሰጣቸው ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በሂደት ላይ እንደሚገኙ ነው የተገለፀው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም