የሴቶች ከ18 ዓመት በታች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን በምስራቅ አፍሪካ የዞን 5 የእጅ ኳስ ውድድር ሁለተኛ ድላቸውን አስመዘገቡ

74

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2011 በምስራቅ አፍሪካ የዞን 5 የእጅ ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች የሴቶች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ ድላቸውን አስመዘገቡ።

የዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን(አይ.ኤች.ኤፍ) የሚያዘጋጀው ውድድር ከትናንት በስቲያ በዛንዚባር መጀመሩ ይታወቃል።

በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያ ከ18 እና 20 ዓመት በታች በሁለት ብሔራዊ ቡድኖች ተወክላለች።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ ለኢዜአ እንደገለጹት ትናንት በውድድሩ ሁለተኛ ቀን ውሎ የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች የሴቶች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን የቡሩንዲ አቻቸውን 14 ለ 13 ማሸነፍ ችሏል።

ውጤቱን ተከትሎ ብሔራዊ ቡድኑ ሁለተኛ ድሉን ያስመዘገበ ሲሆን ከትናንት በስቲያ በውድድሩ መክፈቻ ቀን ጅቡቲን 52 ለ 3 ሰፊ የግብ ልዩነት መርታቱ የሚታወስ ነው።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን ትናንት ሁለት ጨዋታዎችን ተጫውተው እንደነበርም አቶ ሞላ ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረት ጠዋት ከኬንያ ጋር የነበረቸውን ጨዋታ 26 ለ 12 መሸነፋቸውንና ከሰዓት በነበራቸው ጨዋታ ደግሞ የታንዛንያ አቻቸውን 23 ለ 14 እንዳሸነፉም ገልጸዋል።

ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑ በምድብ አንድ ከኬንያ፣ ታንዛኒያና ሩዋንዳ ጋር መደልደሉ ይታወቃል።

የምስራቅ አፍሪካ የዞን 5 የእጅ ኳስ ውድድር እስከ መጋቢት 9 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል።

በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኡጋንዳ፣ ጅቡቲ፣ ቡሩንዲ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳና ኬንያ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም