በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተጭበረበረ መታወቂያ ለሌሎች ተማሪዎች ሲፈተኑ የተገኙ ሁለት ግለሰቦች ተያዙ

59
ጎንደር ግንቦት 23/2010 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በተጭበረበረ መታወቂያ ለሌሎች ተማሪዎች ሲፈተኑ የተገኙ ሁለት ህገወጥ ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡ የምሪያው ኃላፊ አቶ መስፍን እርካቤ ለኢዜአ እንደተናገሩት ግለሰቦቹ የተያዙት ዛሬ ጠዋት እየተሰጠ ባለው የፊዚክስ ትምህርት የፈተና መርሀ ግብር ላይ ወደ መፈተኛ ክፍል ገብተው ሲፈተኑ ነው፡፡ በታች አርማጭሆ ወረዳ በራስ አሞራው ውብነህ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ጨርሶ የተቀመጠው ወጣት አምሳሉ ሹምዬ፤ መንበሩ ደረሰ ለተባለው የ10ኛ ክፍል ተፈታኝ በህገወጥ መታወቂያ ሲፈተን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ በተመሳሳይ በጭልጋ ወረዳ በአይከል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አየነው ሁነኛው የተባለ የ12ኛ ክፍል ተማሪ አዳነ ታረቀኝ ለተባለ የ10ኛ ክፍል ተማሪ በተጭበረበረ መታወቂያ ገብቶ ሲፈተን መያዙን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ እንደኃላፊው ገለጻ፣ ግለሰቦቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ሲሆን፣ በቀጣይ አግባብ ላለው የፍርድ አካል ቀርበው ቅጣት እንደሚተላለፍባቸው ይደረጋል፡፡ አንዳንድ ስነ-ምግባር የጎደላቸው ተፈታኞች በተጭበረበረ መንገድ ለመፈተን የሚያደርጉት ጥረት ፈተናዎችን የሚያደናቅፉና ሌሎች ተፈታኞችንም ችግር ላይ የሚጥል በመሆኑ ተፈታኝ ተማሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኃላፊው አሳስበዋል፡፡ በዘንድሮ የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በዞኑ በ42 ትምህርት ቤቶች 26ሺህ 800 የመደበኛና የግል ተፈታኝ ተማሪዎች ፈተናውን በመውሰድ ላይ ናቸው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም