ክልል አቀፉ የደኢህዴን አመራሮች መድረክ ተጠናቀቀ

65

ሀዋሳ መጋቢት 4/2011 የደቡብ ኢትዮጵያ ህዘቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/ አመራሮች  የውይይት መድረክ ተጠናቀቀ፡፡

የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት የገጠር ፖለቲካና ድርጅት ስራዎች ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደ ሚካኤል ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በሰጡት መግለጫ መድረኩ የተለያዩ የስራ ክንውኖችን መገምገሙን አመልክተዋል።

በቅርቡ የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ በአርባምንጭ ያካሄደውን ግምገማ ተከትሎ የተካሄደ እንደሆነም ገልፀዋል።

በመድረኩ ክልላዊና እና ሀገራዊ  ወቅታዊ ሁኔታዎች  እንዲሁም የስድስት ወራት የድርጅቱ የስራ አፈጻጸም መገምገሙን አስታውቀዋል።

"በመድረኩ የተቀመጡ አቅጣጫዎች  ለመላው የክልሉ አመራር ለማሳወቅ የተዘጋጀው ክልል አቀፍ መድረክም የጋራ መግባባት የተደረሰበት ነው" ብለዋል።

አቶ ስንታየሁ እንዳሉት  በመድረኩ ጎልተው የወጡ  የአደረጃጀት ጥያቄዎች  የክልሉን ህዝቦች አንድነትና ጥቅም የማይጎዳ ፣ ሃገራዊ ነባራዊ ሁኔታ እንዳገናዘበና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ተከትሎ እንዲፈፀም ድርጅቱ ድርሻውን ይወጣል።

" አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ ደኢህዴን የክልልና ሌሎች የአደረጃጀት ጥያቄዎችን አፍኗል የሚለው አስተሳሰብ የተሳሳተ ነው" ብለዋል።

በዚህ ምክንያት ክልል አቀፍ መድረኩ መቋረጡን አስታውሰው የተወሰኑ አመራሮች ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸው ተገቢነት የሌለው እንደሆነ ተገምግሞ መድረኩ መቀጠሉን ጠቁመዋል።

በመድረኩ ያለፉት ስድስት ወራት የመንግስትና የድርጅት ስራዎች ግምገማ  መሰረታዊ የመልካም አስተዳደርና የህዝብ ጥያቄዎች የሚፈቱበት አቅጣጫ ተቀምጧል።

ተመሳሳይ መድረኮች  እስከ ቀበሌ ድረስ በማካሄድ  በጉድለት የተለዩ ጉዳዮች ፣ መንስኤዎችና የሚፈቱበት አግባብ ላይ ውይይት እንደሚደረግ  አቶ ስንታየሁ አስታውቀዋል።

በመድረኩ  1 ሺ 900 የደኢህዴን  አመራሮች መሳተፋቸው ታውቋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም