ለውጡ ወደ ታች ባለመውረዱ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ የምስራቅ አማራ ወጣቶች ገለጹ

46

ወልድያ መጋቢት 4/2011 በሃገር አቀፍም ሆነ በክልል አቀፍ ደረጃ ተስፋን ይዞ የመጣው ለውጥ  ወደ ታች ባለመውረዱ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ የምስራቅ አማራ  ወጣቶች ገለጹ፡፡

" በወጣቶች የነቃ ተሳትፎ የተጀመረውን ለውጥ በማጠናከር የሕዝባችንን ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን" የሚል  መሪ ሃሳብ በወልድያ ከተማ ውይይት ተካሄዷል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የወልድያ ከተማ ነዋሪ ወጣት አብዲ አህመድ እንደገለፀው በአዴፓ ከታች እስከላይ ያሉ አመራሮች ለረጅም ጊዜ በሥልጣን ላይ የቆዩና የሚበቃቸው  በመሆናቸው እንደ አቶ ገዱ ሥልጣናቸውን ለወጣቱ ሊያስተላልፉ ይገባል፡፡

ነባሩ አመራር የችግሩ ስፋት ገብቶት ለወጣቱ ስራ ፈጣሪነት መፍትሄ መስጠት እንደተሳነውም ተናግሯል፡፡

ከደቡብ ወሎ ዞን የመጣው ወጣት አሸናፊ ፈንታው በበኩሉ የክልሉ ንብረት የሆነው አብቁተ በቢሮክራሲ ውጣውረድና በወለድ ብዛት ስራ ፈጣሪው ወጣት ብድር ወስዶ እንዳይሰራ እንቅፋት መሆኑን ተናግሯል፡፡

" አትችሉም አትመጥኑም ተብለው በሕዝብ ተገምግመው የወረዱ አመራሮች ተመልሰው በተለያየ አመራር እንዲሰሩ መደረጉ የጠራ አመራር እንዲኖር ሕዝቡ የሚያደርገውን ትግል እያበላሸ ነው" ብሏል፡፡

ከዋግ ህምራ አስተዳደር ዞን  የመጣው ወጣት ደሳለኝ በዛብህ በሰጠው በሀገሪቱ  የመጣው  ለውጥ ወደ ሕዝቡ ባለመውረዱ ወጣቱ የራሱን ገቢ አፍርቶ ተጠቃሚ እንዳይሆን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

በአካባቢው እየታየ ያለው የሰላም ማጣት ስጋት ተወግዶ ወጣቱ ወደ ልማት እንዲሰማራ የሁለቱ ክልሎች አመራሮችና ሕዝቡ ችግሮችን በውይይት እንዲፈቱም ጠይቋል፡፡

የዋግ ህምራ ዞን ሕዝብ ለደርግ መወገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢያደርግም በመንገድ፣ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎችም ልማቶች ወደ ኋላ የቀረ በመሆኑ መንግሰት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስቧል፡፡

ውይይቱን የመሩት የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር  አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዳሉት ወጣቱ አሁን እየገጠሙት ባሉት ጊዜያዊ ችግሮች ተስፋ ሳይቆርጥ ተስፋ ሰንቆ ሊንቀሳቀስ ይገባል፡፡

" በወጣቱ የፀና ትግል የመጣ ለውጥ አለ " ያሉት አቶ ገዱ አሁን ላይ ለውጡ እንዲቀለበስ አልመው የሚሰሩ አካላትም መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

"በመስዋእትነት የመጣው ለውጥ ባጭር ጊዜ ነፃነትን ያጎናጸፈና መብታቸው ተነፍጎ በስደት የነበሩ ዜጎችን የመለሰና ለዜጎች የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ነው "ብለዋል፡፡

በህዝብ ቀና ትግል የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ የሚሰሩ አክራሪ ፖለቲከኞችንና ሥልጣን ያጡ ቡድኖችን ሴራ በማክሸፍም ወጣቱ የለውጡን ቀጣይነት ማረጋገጥ እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

ሕዝቡ ከመንግስት ጋር ሆኖ ሰላምንና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከሰራ በሕዝቡ ፍላጎት የመጣ ለውጥ ነውና ወደታች የማይወርድበት ምንም ምክንያት እንደሌለ አስረድተዋል፡፡

የወጣቱን ሥራ ፈጣሪነት ለማጠናከርም ክልሉ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር በጀት መመደቡንና እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አቶ ገዱ አስታውቀዋል፡፡

በውይይቱ ከምስራቅ አማራ የተወጣጡ  ከ600 በላይ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም