እንደ አዲስ ብቅ እያሉ ያሉ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ

431

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2011 በባክቴሪያ፣ በቫይረስና በትላትሎች የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት ለመከላከል በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ።

ይህ የተገለጸው  ‘አፍሪካ ሴንተር ፎር ዲዝዝ ኮንትሮል ኤንድ ፕሪቬንቴሽን’ (አፍሪካ ሲ ዲ ሲ) ባዘጋጀው ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ዓለም አቀፍ  ጉባዔ ላይ ነው።

በሀርቫርድ ዩንቨርሲቲ የፐብሊክ ሄልዝ ትምህርት ቤት ዲን ሚሼል ዊልያምስ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ባለፉት 30 ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተላላፊ በሽታዎች ስርጭት በሶስት እጥፍ ጨምሯል።

በ15 ዓመታት ውስጥ ብቻ ኢቦላ፣ ዚካ፣ ሳርስ፣ ኮሌራ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስና በሌሎች በሸታዎች በሚሊዬን የሚቆጠሩ ሰዎች መጠቃታቸውን ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ተሞክሮ እንደሚያሳይም አገራት ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል በቅድሚያ ዝግጁ ከመሆን ይልቅ በሽታዎች ከተከሰቱ በኋላ ርብርብ የማድረግና ችግሩ ከተፈታ በኋላ ትኩረታቸውን እንደሚቀይሩ አንስተዋል።

ሚሼል ዊልያምስ እንደገለጹት ይህን መሰል አካሄድ የብዙ ሰዎችን ህይወት የሚቀጥፍና በቢሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ወጭ የሚጠይቅ ነው ።

አገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ የተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት ለመከላከልም ዝግጁነቱ አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እ.አ.አ በ2014 የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ የተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት በመከላከል በኩል ያለውን ክፍተት ያመላከተ መሆኑን አንስተዋል።

የአገር ውስጥ የጤና ተቋማት አቅም ማነስ፣ በቂ የሆነ የቁጥጥርና የማስጠንቀቂያ አሰራር ያለመኖር፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ምላሽ የዘገየ መሆንን በምክንያትነት ማማላከቱን አብራርተዋል።

የህዝብ ቁጥር እያደገ መምጣት ፣በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ብዛት መጨመር፣ የሰዎች በተደጋጋሚ የመጓዝ ልምድ መጎልበት፣ ድህነት፣ ጦርነት፣ በአንድ አገር የታየ በሸታ ከሰዓታት በኋላ የሕብረተሰብ ጤና ቀውስ ችግር ሊሆን መቻልም ችግሮች ናቸው።

በመሆኑም በአለም አቀፍ  ደረጃ  የተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት ለመከላከል ቅንጅትና ትብብር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የ’አፍሪካ ሲ ዲ ሲ′ ዳይሬክተር ጆን ንኬንጋሶንግ በበኩላቸው ጉባዔው በዓለም አቀፍ ደረጃ በአዲስ መልክ እየተከሰቱ ያሉና በድጋሚ እያንሰራሩ የሚገኙ እንዲሁም የህብረተሰብ ጤናን አደጋ ላይ የሚጥሉ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ መረጃዎችን ለመለዋወጥ ያስችላል ብለዋል።

በጉባዔው ላይ በተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ላይ አተኩረው የሚሰሩ ኤክስፐርቶች ይሳተፋሉ።

በተጨማሪም በቅርቡ የተከናወኑ የጥናት ውጤቶችን በመጠቀም በተላላፊ በሽታዎች የተያዙ ህሙማንን  በመለየት ህክምና ለመስጠት የሚረዳ መሆኑንም ገልጸዋል። መድረኩ በተላላፊ በሽታዎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለተካዊ ተጽዕኖዎች ላይ ጥልቀት ያለው ውይይት በማድረግም ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑንም አክለዋል።