የአሜሪካው አትሌት ኢን አክሽን የቅርጫት ኳስ አካዳሚ በኢትዮጵያ የወዳጅነት ጨዋታና የስልጠና መርሃ ግብር አዘጋጅቷል

98
አዲስ አበባ ግንቦት 23/2010 የአሜሪካው 'አትሌት ኢን አክሽን' የቅርጫት ኳስ አካዳሚ ከነገ በስቲያ ጀምሮ በኢትዮጵያ የወዳጅነት ጨዋታና የስልጠና መርሃ ግብር አዘጋጅቷል። የወዳጅነት ጨዋታና የስልጠና መርሃ ግብሩን ያዘጋጁት የቅርጫት ኳስ አካዳሚው ከኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽንና ከአዲስ አበባ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ነው። የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይመር ሀይሌ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፤ የአሜሪካው የቅርጫት ኳስ አካዳሚ እስከ ሰኔ 4 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቆይታ ያደርጋል። አካዳሚው በወጣለት መርሃ ግብር መሰረት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ፣ ከቢጂአይ ኢትዮጵያ፣ ከጎንደር ከተማና ከአማራ ህንጻ ዲዛይንና ኮንስትራክሽን ክለቦች ጋር በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ከወልቂጤ ከተማ ጋርም ወልቂጤ ላይ የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል። 'አትሌት ኢን አክሽን' የቅርጫት ኳስ አካዳሚ ከወዳጅነት ጨዋታው በተጨማሪ ለተጫዋቾችና ለአሰልጣኞች የአንድ ቀን መሰረታዊ የቅርጫት ኳስ ስልጠና እንደሚሰጡም ነው አቶ ይመር ያስረዱት። በአዲስ አበባ በሚገኙት የጎሮ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትና የቤተል መካነየሱስ ትምህርት ቤት እንዲሁም በወልቂጤ ከተማ ለሚገኙ የታዳጊ ወጣቶች የቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች አጭር ስልጠና እንደሚሰጥም አክለዋል። የአካዳሚው ተጫዋቾችና አሰልጣኞች በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የወዳጅነት ጨዋታና የስልጠና መርሃ ግብሩን አጠናቀው ሰኔ 4 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ጠቁመዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም