ብሪታኒያ በኢትዮጵያ ለደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ምርምራ አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች – አምባሳደር አልስቴር

571

አዲስ አበባ 4/2011 ብሪታኒያ በኢትዮጵያ ለደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ምርምራው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ በኢትዮጵያ የአገሪቷ አምባሳደር አልስቴር ማክፔል ገለጹ።

መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር የነበረው ንብረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ቢሾፍቱ አካባቢ መከስከሱ ይታወቃል።

የበረራ ቁጥሩ ኢቲ 302 የሆነው ይህ አውሮፕላን 149 መንገደኞችንና 8 የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ በረራ ከጀመረ ከስድስት ደቂቃ በኋላ በመከስከሱ በውስጡ የነበሩ 157 ሰዎች ህይወት አልፏል።

አምባሳደሩ ትናንት አውሮፕላኑ የተከሰከሰበት ቢሾፍቱ አካባቢ በመሄድ ምልከታ ማድረጋቸውን በኢትዮጵያ የብሪታኒያ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የአውሮፕላኑን የአደጋ መንስኤ ለማወቅ ምርምራ ለሚያደርገው ቡድን የብሪታኒያ የአየር አደጋ የምርምራ ተቋም ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አምባሳደር አልስቴር ገልጸዋል።

አደጋውን ተከትሎ ብሪታኒያ አራት የአቪዬሽን ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ የላከች ሲሆን ባለሙያዎቹ ትናንት ጀምሮ በአደጋው ቦታ ያለውን ቡድን እያገዙ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአቪዬሽን ባለሙያዎቹ አስፈላጊውን ድጋፍ ለምርመራ ቡድኑ እንደሚያደርጉም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

አምባሳደሩ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ጋር በመገናኘት በአደጋው ከጎናቸው በተለዩት የስራ ባልደረቦቻቸው ከገጠማቸው ሃዘን እንዲፅናኑ ተመኝተውላቸዋል።

የብሪታኒያ መንግስት በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ የብሪታኒያ ዜጎች ቤተሰቦች እያደረገ ያለውን ድጋፍ አሁንም እንደሚቀጥል አምባሳደሩ ተናግረዋል።

“በዚህ አስከፊ አደጋ ለተጎዱት ሁሉ መጽናናትን እመኛለሁ ወደ አደጋው ቦታ የመጣሁት ብሪታኒያ ኢትዮጵያን ለመደገፍ ያላትን ቁጥርጠኝነት ለማረጋገጥና እና ከምርመራው ሃላፊዎች ጋር ለመነጋገር ነውም” ብለዋል።

አምባሳደር አልስቴር ማክፔል አደጋው በደረሰበት ስፍራ ተገኝተው ለምርምራ ቡድኑ እገዛ እያደረጉ ከሚገኙት የብሪታኒያ የአየር አደጋ የምርምራ ተቋም ባለሙያዎችም ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ትናንት ብሪታኒያ በኢትዮጵያ የተከሰከሰውን ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ተከትሎ ተመሳሳይ አውሮፕላኖች በአየር ክልሏ ላልተወሰነ ጊዜ በረራ እንዳያደርጉ ማገዷ ይታወሳል።