ኢትዮጵያና ፈረንሳይ የህዋን ሳይንስ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

99

አዲስ አበባ  መጋቢት 4/2011 ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በህዋ ሳይንስ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ እና የፈረንሳዩ ብሔራዊ የስፔስ ጥናት ማዕከል ተጠሪ ዶክተር ጄን-የቭስ ሊ ጋል ናቸው። 

ስምምነቱ ከሳተላይት የሚገኙ የአየር ንብረት መረጃዎችንና መተግበሪያዎችን በመጠቀም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅኖዎችን በዘላቂነት ለመቆጣጠር የጋራ ክትትል ለማድረግ  እንደሚያስችል ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።

ስምምነቱ የህዋ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እርሻን፤ የደን ሽፋንን፤ ውሃ የሚገኝባቸውን አካባቢዎችን ለመለየትና መከታተል የሚያስችል እንዲሁም ሌሎች ተግባራትንም በጋራ ለመስራት የሚያግዝ ነው።

የሰው ሃይል አቅም ግንባታና ልውውጥ፤ የህዋ ሳይንስን ለሰላማዊ ግልጋሎት መጠቀም የሚያስችል የትብብር ዘርፍ እንዲኖር ማዕቀፍ በመፍጠር ወደ ትግበራ የሚገቡበትን ሁኔታዎችን ማመቻቸትም የስምምነቱ አካል ናቸው።

ኢትዮጵያ በህዋ ሳይንስ ዘርፍ  ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል እየሠራች ትገኛለች።

የአሁኑ ስምምነት በፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የተመራ ልዑክ በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ያደረጉት የትብብር ስምምነት አካል እንደሆነም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በ2009 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በ2017 ዓ.ም ከስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማት ተጠቃሚነቷ የጎለበተ እና ለዘርፉ እድገት የራሷን አስተዋጽኦ የምታበረክት ኢትዮጵያን ማየት ራዕዩ አድርጎ በመስራት ላይ ይገኛል።

በአንጻሩ የፈረንሳዩ ብሔራዊ የስፔስ ጥናት ማዕከል እ.አ.አ በ1961 የተቋቋመ ሲሆን ለወደፊት በህዋ ሳይንስ ስርአት ጠቃሚ የሆኑ ሀሳቦችን ማፍለቅ፣ የመጨረሻውን የህዋ ቴክኖሎጂ መጠቀምና ፈረንሳይ ያለ ምንም ቁጥጥር ለህዋ ተደራሽ እንድትሆን የማድረግ ሃላፊነት ተሰጥቶት እየሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም