በሕጻናት ላይ የሚደርስውን የመቀንጨር ችግር ለማስወገድ እንደሚሰራ የጤና ጥበቃ ሚኒሰትሩ አስታወቁ

137

ሰቆጣ መጋቢት 4/2011 በኢትዮጵያ ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን የመቀንጨር ችግር ለማስወገድ በቅንጅት እንደሚሰራ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ገለጹ።

የፌዴራል መንግሥት ሚኒስትሮችና የአማራ ክልል የቢሮ ኃላፊዎች ቡድን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት አፈጻጸም የመስክ ምልከታ አካሂዷል፡፡

ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በመስክ ምልከታው እንደገለጹት ስምምነቱ በአማራና በትግራይ ክልሎች በተመረጡ 33 ሞዴል ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ ነው።

በሰቆጣ ስምምነት የትምህርት ቤት ምገባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ ወተት፣ እንቁላልና መሰል አልሚ ምግብ በራስ አቅም ለመቻል በሙከራ ደረጃ  እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በወረዳዎቹ ያጋጠሙ ችግሮችን በዝርዝር በመለየትም አፋጣኝ ማሰተካከያ እንደሚደረግ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

ስምምነቱን የፈረሙት አምስት አግባብ ያላቸው መሥሪያ ቤቶች የጋራ እቅድ ከማዘጋጀት ጀምሮ ወጥ የሆነ የበጀትና ሪፖርት ሥርዓት እንደሚፈጥሩ አስረድተዋል።

የስምምነቱ የአማራ ክልል አስተባባሪ አቶ ተፈራ ቢራራ  የመቀንጨርን ችግሩን በክልሉ አቅም ብቻ ስለማይፈታ የመሥሪያ ቤቶቹ እገዛ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የአካባቢውን መልከዓ ምድርና ነባራዊ ሁኔታን መሠረት በማድረግ ችግሮችን ለመፍታት የሚከናወኑትን ተግባራት መጎብኘታቸው ለሥራቸው ስኬታማነት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የቢግ ዊን ግብረ ሰናይ ድርጅት አስተባባሪ ዶክተር ከሰተ ብርሃን አድማሱ በኢትዮጵያ የመቀንጨር ችግር ለማስወገድ በመንግሥት የተያዘውን ሥራ እንደሚያግዙ  አረጋግጠዋል።

በጉብኝቱ የጤና፣የትምህርት፣የግብርናና የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሮች  እንዲሁም የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶችና የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይና  የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ዴኤታዎችና የክልሉ አግባብ ያላቸው ቢሮዎች ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የግብርና ሰርቶ ማሳያ ጣቢያዎችና የዛፍ ጥላ ትምህርት ቤቶች የጉብኝቱ አካል ነበሩ።

በኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በታች የሚገኙ ሕጻናት የሚደርስባቸውን የመቀንጨር ችግር በ2020 ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ሁሉም ክልሎች በ2007 በሰቆጣ መፈረማቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም