እነ ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው ተሻሻሎ በቀረበባቸው ክስ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

122

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2011 በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ክስ የተመሰረተባቸው እነ ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው ተሻሻሎ በቀረበባቸው ክስ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ።

የቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ ስምንት ሰዎች ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በመስጠት የተመሰረተባቸው ክስ እንዲሻሻል የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የካቲት 26 ቀን 2011 ዓ.ም ትእዛዘ መስጠቱ ይታወሳል።

”የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ባላስተማራቸውና ባልተቀረጸ ሥርዓተ ትምህርት ሐሰተኛ የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ እንዲሰጥ አድርገዋል” በተባሉ ስምንት ተጠርጣሪ የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ (ሜቴክ) የስራ ሃላፊዎች ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ መመስረቱ ይታወቃል።

በአሜሪካ አገር ከሚታወቀውና በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ አንዱ ከሆነው ‘ካሊፎርኒያ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ’ ጋር ተቀራራቢ ስም ያለው ተቋም፤ ሆኖም ግን በማንም ዘንድ የማይታወቅ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ለማስተማር ዶክተር መኮንን ገብረሚካኤል ለተባለ ተጠርጣሪና በቁጥጥር ስር ካልዋለ አንድ ግለሰብ ጋር ሐሰተኛ የትምህርት ተቋሙ እንደተከፈተ የዐቃቤ ህግ ክስ ያስረዳል።

ተጠርጣሪው ዶክተር መኮንን ገብረሚካኤል ራሳቸውን የትምህርት ተቋሙ ሥራ አስኪያጅ አድርገው በማቅረብ፣  ከቀድሞ የሜቴክ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በጥቅም በመመሳጠር በሐሰተኛ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ስም ከሜቴክ ጋር ለማስተማር የውል ስምምነት መፈራረሙንና የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው ማጽደቃቸውን የዐቃቤ ሕግ ክስ አመልክቷል።

ከሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው በተጨማሪ ብርጋዴር ጄነራል ጥጋቡ ፈትለ፣ ሻለቃ ገብረሥላሴ ገብረጊዮርጊስ፣ ሻለቃ ፋሲል አበራ፣ መቶ አለቃ ቶማስ ደረሰ፣ ወሰንየለህ ኃይለሚካኤል እና ሀድአት ወልደትንሳይ ከሐሰተኛ ትምህርት ተቋሙ ጋር በተያያዘ የውል ስምምነት በመፈራረም ተጠርጥረዋል።

በዚሁ የክስ መዝገብ ላይ 1ኛ ተከሳሽ ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኛው የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲሰሩ ማርዳ መለስ ለተባለች ግለሰብ የማይገባ ጥቅም ለማስገኝት በማሰብም ከ57 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በላይ ገንዘብ እንዲከፈላት አድርገዋል በሚል ሁለተኛ ክስ ተመስርቶባቸውል።

በመሆኑም የፌዴራሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትእዛዝ መሰረት ዛሬ ክሱን አሻሻሎ በማቅረቡ ተከሳሾቹ ምላሻቸውን ለመጋቢት 9 ቀን 2011ዓ.ም እንዲያቀርቡ ነው ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም