ፕሬዚዳንት ማክሮን አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር ትሻለች አሉ

452

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2011 የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደምትሻ ገለፁ።

ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በኢንቨስትመንት፣ በኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ወታደራዊ መስኮችና በቅርስ ጥበቃ የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።

ለሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ለክፍለ ዘመናት የዘለቀ ወዳጅነት ዳግም እንዲያንሰራራ ትሻለች ብለዋል።


የፈረንሣዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ያደረጉትን ቆይታ አስመልክቶ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር የሰጡት መግለጫ

የሁለቱን አገራት ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ስምምነቶች እንደተደረጉ የገለፁት ፕሬዚዳንቱ የአገራቱ ትብብር በሁሉም መስክ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

“ፈረንሳይ መተው በጠየቁን መሰረት በተለያዩ ዘርፎች የትብብር ስምምነት ተፈራርመናል። በተለይ በመከላከያና በደህንነት የጋራ ስምምነት ተፈራርመናል። ይህ ትብብር አየር ኃይልና ባህር ኃይል፣ ጦር ኃይል እንዲጠናከር ያደርጋል በስልጠናም ሆነ በቁሳቁስ ድጋፈ እናደርጋለን ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሚና በአፍሪካም ሆነ በምስራቅ አፍሪካ ትልቅ ነው። የኢትዮጵያን ሚናም እናደንቃለን ሰላም በማስከበር ሽብርተኝነትን በመዋጋት እያደረገች ያለውን ጥረት ማገዝ እንፈልጋለን። እርሶ ወደ ሥልጣን ከመጡ የጀመሩትን አገራዊ ለውጥ እኛም ተመሳሳይ ራዕይ ስላለን ለመደገፍ ዝግጁ ነን። “

ፕሬዝዳንቱ በኢንቨስትመት መስክ በርካታ የፈረንሳይ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማድረግ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች እንዳሉም ገልጸዋል።

በቅርቡም የተወሰኑ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስራ መጀመራቸውን አውስተዋል።

በፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ በኩል 85 ሚሊየን ዩሮ በብድር መልኩ እንዲሁም 15 ሚሊየን ዩሮ ደግሞ በኢትዮጵያ የተጀመሩ ለውጦችን ለመደገፍ እንደሚሰጥም ፕሬዝዳንት ማክሮን አረጋግጠዋል።

ፈረንሳይ በቋንቋና ትምህርት ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳላትም እንዲሁ።

ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደቶች ላይ በመሆኗ የሚያጋጥሙ የሰላም መደፍረስ ችግሮችን ለመፍታት ፈረንሳይ የበኩሏን ድርሻ ለማበርከት ፈረንሳይ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላትም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላም እንዲሰፍንና ቀጠናዊ ትብብሩ እንዲጠናከር የምታደርገውን ጥረት ያደነቁት ፕሬዝዳንት ማክሮን አገራቸው በዚህ ዙሪያ የማገዝ ፍላጎት እንዳላትም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው ፤ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ያላቸውን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ መነጋገራቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ጠንካራ የሆነ የባህር ሀይል እና የአየር ሀይል ለመገንባት ፍላጎት እንዳላት የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ ፈረንሳይ በአውሮፓ ጠንካራ የመከላከያ ኃይል አላቸው ከሚባሉ አገራት አንዷ በመሆኗ የስምምነቱ ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

ፈረንሳይ ከአንድ መቶ ዓመታት በፊት የሰራችው የአዲስ አበባ ጅቡቲ መንገድ ለረዥም ዘመናት ማገልገሉን ገልጸው ኢትዮ-ፈረንሳይ በጋራ ለመስራት የደረሷቸው ስምምነቶችም ረጅም ዘመናትን የሚዘልቁ እንዲሆኑ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በወታደራዊ መስክ የሚኖረው ግንኙነት ጠንካራ የባህር ሃይል እና የአየር ሃይል ከመገንባት እስከ ኒኩለር ማብላያ ግንባታ የሚደርስ መሆኑንም ተናግረዋል።

“በኢትዮጵያ ታሪክ ጥንታዊ ስልጣኔ እክብሮትና አድናቆት ያላቸው እና ያንን የነበረውን ለመመለስ ለመጠበቅ በሚደረግ ጥረት ሁሉ የበኩላቸውን አስተዋፆ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው አይተናል። ለዚህም በኢፌዴሪ መንግስት ምስጋና ያቀርባል። በተጨማሪም በቀጠናው ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ጠንካራ የመከላከያ ኃይል መገንባት ትፈልጋለች  በተለይ በአየር ኃይልና ባህር ኃይል ከፈረንሳይ መንግስት ጋር ተባብረን ጠንካራ አየርና ባህር ኃይል ለመገንባት ላለው ፍላጎት ፕሬዚዳንት ማክሮን በሁሉም መስክ ድጋፍ ለማድረግ ከእኛ መከላከያ ጋር ለመስራት የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።ይህም ከአውሮፓ አገራት ጋር ከሚደረገው ሁለትዮሽ ግንኙነት እንደ አንዱ ሊወሰድ ይችላል “

ፕሬዚዳንት ማክሮን በኢትዮጵያ መንግስት የተደረገላቸውን የስራ ጉብኝት ግብዣ ተቀብለው በመምጣታቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን  ትላንት ምሽት በብሄራዊ ቤተመንግስት በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የእራት ግብዣ ተደርጎላቸዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን የገለፁት ፕሬዚዳንት ማክሮን ለተጎጂ ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል።

ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ ጉብኝትን ዛሬ ካጠናቀቁ በኋላ በናይሮቢ በሚካሄደው የአንድ ፕላኔት የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1897 መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።