ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በተለያዩ መስኮች ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

95

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2011 ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በተለያዩ መስኮች በትብብር ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።

በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙትን የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በላልይበላ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ለፕሬዚዳንት ማክሮን ክብር ሲባልም ዘጠኝ ጊዜ መድፍ ተተኩሷል።

ከአቀባበሉ በኋላ ዛሬ ማምሻውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተካሄደ የስምምነት ፊርማ ስነስርዓት ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በተለያዩ መስኮች በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን አረጋግጠዋል።

ሁለቱ መሪዎች በተወካዮቻቸው በተፈራረሙት ፊርማ ፈረንሳይ የላልይበላ አብያተ ክርስቲያናት ቅርስን  የሙያና የገንዘብ ድጋፍ ታደርጋለች።

ከዚህ በተጨማሪም በኢንቨስትመንት፣ በመከላከያ ሃይል አቅም ግንባታ በተለይም በባህርና በአየር ሃይል ፈረንሳይ ድጋፏን ለማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተደርጓል።

ሁለቱ መሪዎች ለሚዲያ በሰጡት የጋራ መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ያላቸውን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ መነጋገራቸውን ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ማክሮን በኢትዮጵያ መንግስት የተደረገላቸውን የስራ ጉብኝት ግብዣ ተቀብለው በመምጣታቸው ዶክተር አብይ አመስግነዋል።

በጉብኝቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በፈረንሳይ በነበራቸው ጉብኝት ወቅት የተደረሰውን ስምምነት ወደተግባር ማስገባት በሚቻልበት ሁኔታ መምከራቸውንም ጠቁመዋል።

ፕሬዚዳንት ማክሮን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ወደቀድሞ ገናናነቷ ለመመለስ የምታደርገውን ጥረት ፈረንሳይ የምትደግፍ መሆኗን ገልጸዋል።

አገራቸው ለኢትዮጵያ የገንዘብ ብድርና ድጋፍ እንደምታደርግም ተናግረዋል።

የፈረንሳይ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚሰሩ መሆናቸውን ገልጸው በአሁኑ ጉብኝታቸው ባለሃብቶችን ይዘው መምጣታቸውን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ በሞቱት ሰዎች የተሰማቸውን ሃዘንም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያና ፈረንሳይ በመካከላቸው ያለው የኢኮኖሚ ትስስርም እየጎለበተ መምጣቱን ከፈረንሳይ ኤምባሲ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ፈረንሳይ የትራንስፖርት ቁሳቁሶችና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ወደ ኢትዮጵያ ስትልክ ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን በተለይም ቡና ትልካለች።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለሶስት ሺህ ዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ 30 የፈረንሳይ ኩባንያዎች አሉ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከአምስት ወራት በፊት በአውሮፓ በተለያዩ አገሮች ጉብኝት ሲያደርጉ ከጎበኟት አገር መካከል ፈረንሳይ አንዷ ስትሆን ከፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ይታወቃል።

ከነዚህም መካከል በአለም አቀፍ መድረክ አንድ በሚያደርጓቸው አጀንዳዎች፣ በጸረ ሸብር፣ በአየር ንብረትና በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስት (ኢጋድ) በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።

ፈረንሳይ በኢትየጵያ በሚገኘውን ኤምባሲዋን ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ፣ በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለማደስ የሚያስችል የገንዘብና የባለሙያ እገዛና ድጋፍ ለማድረግ ሌላው ከስምምነት ከደረሱባቸው ነጥቦች መካከል ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም