በሃገሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተቀናጀ የግብርና ቴክኖሎጂ ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ ነው

98

አዳማ መጋቢት 3/2011 በሃገሪቱ የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የተቀናጀ የግብርና ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን  የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምርምርና ኤክስቴንሽን ተቋማት ግንኙነት የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

በሚኒስቴሩ የእርሻ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ  በመድረኩ እንዳሉት ለምግብ ዋስትናና ምጣኔያዊ እድገት የግብርና ቴክኖሎጂ የማመንጨት አቅም በቀጣይነት  መገንባት ያስፈልጋል።

በሀገሪቱ በዓመታዊ ሰብል ከሚለማው መሬት 30 በመቶ ብቻ በምርጥ ዘር የሚሸፈን በመሆኑ ምርታማነት በሚፈለገው ደረጃ እንዳያድግ ማነቆ መሆኑን ተናግረዋል ።

" የግብርና እድገቱን በላቀ ደረጃ ሊያስቀጥሉ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች በእጃችን ላይ አሉ፤ ዳገት የሆነብን በተቀናጀና አሳታፊ በሆነ አግባብ አለመስራታችን ነው" ብለዋል።

ከ70 እስከ 80 በመቶ የሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት የተመሰረተው በግብርና ምርት ላይ መሆኑን ጠቅሰው  ይበልጥ ተወዳዳሪ ለመሆን የቴክኖሎጂ አቅምን በመገንባት በጥራት፣በዓይነትና በብዛት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለዚህም  ስኬት በሁለተኛው የእደገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የትግበራ ዘመናት ከልማት አጋሮች ከተገኘው 250 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው ለምርምር ዘርፍ መመደቡን ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል።

ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ በምርምር የሚወጡ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ስርጭት ሂደት ፈጣንና ወቅቱን የጠበቀ በማድረግ የግብርናው ዘርፍ ለማዘመን እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

አቶ ሳኒ እንዳሉት የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ለማረጋገጥ ፣ ለግብርና ኢንዱስትሪዎች ግብዓትነትና ለወጪ ንግድ አቅርቦት የሚውል የግብርና ምርቶችን በስፋት ለማምረት ዩኒቨርስቲዎችን፣የምርምር ማዕከላትንና አርሶ አደሮችን ያሳተፈ የተቀናጀ የግብርና ቴክኖሎጂ ስርጸት ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸው  ካለፈው ዓመት ወዲህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምርምርና ኤክስቴንሽን ተቋማት ግንኙነት በመመስረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከተመረጡ አምስት ዩኒቨርሰቲዎችና  ከአራቱ የክልል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቶች  ጋር በመቀናጀት አዳዲስና ውጤታማ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ወደ ተጠቃሚዎች ዘንድ እንዲደርሱ ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

"ይህም በሀገሪቱ በግብርና ዙሪያ እየተሰጡ ያሉ ትምህርቶች፣ የሚካሄዱ የምርምር ስራዎችን እንዲሁም የግብርና ኤክስቴንሽን ሂደቱን ለማጠናከር ይረዳል" ብለዋል።

በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሶሾ-ኢኮኖሚክ ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ጠሃ ሙሜ  ኢንስቲትዩቱ ከክልሉ የተለያዩ ዞኖች በተመረጡ ዘጠኝ ወረዳዎች ውስጥ  በምርምር የወጡ የተሻሻሉ አሰራሮችን ለአርሶ አደሩ ለማዳረስ  እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም