በሕብረተሰቡ ጎጂ ባህል ምክንያት የጨቅላ ሕጻናትን ሞት መቀነስ አልተቻለም

100

ባህር ዳር መጋቢት 3/2011 በኢትዮጵያ የጨቅላ ህጽናትን ሞት ለመቀነስ ቢሰራም በሕብረተሰቡ ጎጂ ባህል ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ መቀነስ አለመቻሉን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጨቅላ ህጻናት ሞት ምክንያቶች፣ አሁን ያለበት ደረጃና መቀነስ በሚቻልበት መንገድ ላይ ያተኮረ ውይይት በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ ላይ የተገኙት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጨቅላ ህጻናት ጤና አስተባባሪ ዶክተር አብረሃም ታሪኩ እንደገለጹት በኢትዮጵያ በየዓመቱ ሦስት ሚሊዮን ህጻናት ይወለዳሉ፤ ከነዚህም 89 ሺህ የሚሆኑት ለሞት እየተዳረጉ ነው።

ያለ ቀን በመወለድ፣ በመታፈንና እስከ አንድ ወር ባለው የጨቅላ ዕድሜያቸው በሚያጋጥማቸው የተለያዩ በሽታዎች ምክንያት ለሞት እየተዳረጉ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

ያለቀናቸው የሚወለዱ ህጻናት የሚያስፈልጋቸውን በቂ የሙቀት መጠን እንዲያገኙ የካንጋሮ እናት የልጅ እንክብካቤ ወይም ልጅን በደረት ማቀፍ በዓለም አቀፍ ጭምር አይነተኛ መፍትሄ መሆኑን ገልጸዋል። 

ይሁንና "ልጅን በደረት ማዘል የኢትዮጵያዊነት መገለጫ አይደለም" በሚል በሕብረተሰቡ ላይ ያለው አጉል ባህል ምክንያት ጨቅላ ህጻናት የሚያስፈልጋቸውን ሙቀት እንደማያገኙና በእዚህ ምክንያት ለሞት እየተዳረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

"በተጨማሪም ጨቅላ ህጻናት ሲታመሙ ወደ ህክምና ተቋም ይዞ መሄድ ሲገባ ህጻናትን ለሰው ማሳየት መጥፎ ነው ከሚል አስተሳሰብ በመነሳት በባህላዊ መንገድ ለማሳከም በሚደረገው ጥረትም ህጻናቱ እየሞቱ ነው" ብለዋል።

በየቀኑ 250 ጨቅላ ሕጻናት ለሞት እንደሚዳረጉ የተናገሩት ዶክተር አብረሀም "ይህም ከሚወለዱ አንድ ሺህ ህጻናት መካከል 29ኙ ለሞት እንደሚዳረጉ ያሳያል" ብለዋል።

ከሦስት ዓመት በፊት በሀገሪቱ የነበረው የጨቅላ ህጻናት ሞት ምጣኔ አሁንም ተመሳሳይ በሚባልበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከሚወለዱ 1ሺህ ህጻናት መካከል የሚሞቱትን  ጨቅላ ህጻናት ቁጥር ወደ 11 ለማድረስ ላለፉት ሦስት ዓመታት ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራም አሁን ባለው ውጤት ዕቅዱን ማሳካት እንደማይቻል ተናግረዋል።  

ዶክተር አብርሀም አንዳሉት ከአምስት አመት በፊት እንደ ሀገር የጨቅላ ህጻናት ሕክምና በስምንት ጤና ተቋማት ላይ ብቻ ቢሰጥም በአሁኑ ወቅት በ190 ተቋማት አገልግሎቱ እየተሰጠ ነው።

"በቀጣይ አንድ ዓመት ተጨማሪ 80 የጤና ተቋማት የጨቅላ ህጻናት ሕክምና እንዲሰጡ ለማድረግ የሕክምና መሳሪያዎች ተገዝተው በመጓጓዝ ላይ ናቸው" ብለዋል።

በኢትዮጵያ የህጻናትን ሞት መቀነስ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ እያማከረ ያለው የአሜሪካው “ኢሞሪ ዩኒቨርሲቲ" የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር  አብረሃም ገብረማሪያም በበኩላቸው የጨቅላ ህጻናት ሞትን ለመቀነስ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መቅደም አንዳለበት ተናግረዋል።

"መንግስት የጤና ፖሊሲዎችን ከማስቀመጥ ባለፈ በአግባቡ እንዲተገበሩ በማድረግ በኩል ያሉበትን ክፍተቶች መቅረፍ ይኖርበታል" ብለዋል።

የአማራ ክልል  ጤና ጥበቃ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሕይወት ደበበ በበኩላቸው ክልሉም የጨቅላ ህጻናት ሞት የሚስተዋልበት በመሆኑ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በጤና ባለሙያዎች አማካኝነት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

"ሕብረተሰቡም በጤና ባለሙያዎች አማካኝነት የሚነገረውን ምክረ ሃሳብ ተቀብሎ ተግባራዊ በማድረግ ልጆቹን ከሞት ለመታደግ ተባባሪ ሊሆን ይገባል" ብለዋል።

በአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ አዘጋጅነት በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ባለው የውይይት መድረክ ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን በመድረኩም የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የፌዴራልና የክልል አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም