የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ የድህረ ምረቃ መርሐ ግብር ጀመረ

61

መቀሌ መጋቢት 3/2011 በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ሥር የሚገኘው የእንስሳት ሕክምና ኮሌጅ በአግሮ ፕሮሰሲንግ የድህረ ምረቃ መርሐ ግብር ዛሬ ጀመረ።

ኮሌጁ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት 60 ተማሪዎችን ለመቀበል ተዘጋጅቷል።

የዩኒቨርሲቲው እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ ዲን ዶክተር አብርሃ ብስራት እንዳስረዱት ኮሌጁ 18 ተማሪዎችን ለሁለተኛና ለሦስተኛ ዲግሪ በተቀበለበት ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት መርሐ ግብሩ የተጀመረው በዘርፉ ያለውን የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት ነው።

መርሐ ግብሩ በወተትና ወተት ተዋፀኦ፣በሥጋና በሥጋ ውጤቶች፣በማርና በሰም ማቀነባበር ላይ ያተኩራል ብለዋል።

ስልጠናውም  በአብዛኛው ተግባር ተኮር እንደሚሆንም አመልክተዋል።

ኮሌጆቹ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት በሁለተኛ ዲግሪ 40፣ በዶክትሬት ዲግሪ ደግሞ 20 ሰልጣኞችን ለመቀበል ማቀዱንም ዲኑ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይለሥላሴ ወረስ እንዳሉት ኮሌጁ መርሐ ግብሩን የጀመረው በአገሪቱ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ተወዳድሮ ብልጫ በማግኘቱ ነው።

ዩኒቨርሲቲው በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በግሉ ዘርፍ ያለውን የሰው ኃይል እጥረት ለመሸፈን ከባለድርሻ አካላት በተለይም ደግሞ ከተቋሙ ጋር ተቀናጅቶ እንዲሰራ አሳስበዋል።

መርሐ ግብሩ ሰርተው የሚያሰሩ፣ ጥራትና ብዛት ያላቸው ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚያስችል እምነታቸውን ገልጸዋል።

''በዘርፉ ያለውን ከፍተኛ የባለሙያ እጥረት ለልማታችን ማነቆ ሆኖብን ቆይቷል'' ያሉት ደግሞ በየኢትዮጵያ የወተት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ በላቸው ሪሳ ናቸው።

መርሐ  ግብሩ በዘርፉ እሴትን ከመጨመር ባለፈ ኢንዱስትሪ መር ለሆነው የልማት ስትራቴጂ ስኬታማነት እንደሚረዳ ተናግረዋል።

በዘርፉ ለሁለተኛ ዲግሪ  መርሐ ግብር ከተመረጡት ልጣኞች መካከል አንዱ በሰጡት አስተያየት መርሐ ግብሩ የአገሪቱን የወተትና የወተት ተዋጽኦ  በዘመናዊ መንገድ ለማቅረብ ከማስቻሉም በላይ፤ አገሪቱን ከዘርፉ የተሻለ ተጠቃሚ ያደርጋታል ብለዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ከ50 በላይ ምሁራን ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም