ኢትዮጵያ ከእምቅ የተፈጥሮ ሀብቷ ተጠቃሚ አልሆነችም....ዶክተር ካባ ኡርጌሳ

90

ባህርዳር መጋቢት 3/2011 ኢትዮጵያ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ብትሆንም በአግባቡ ባለመልማቱ በሀብቱ ተጠቃሚ አለመሆኗን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ ተናገሩ።

በዘላቂ የውሃና የተፈጥሮ ሃብት አስተዳደር ላይ ያተኮረ ኮንፈረንስ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

ሚኒስትር ዴኤታው በኮንፈረንሱ ላይ እንደተናገሩት መንግስት በ2025 ኢትዮጵያን በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ውጤታማ ሀገር ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

የተፈጥሮ ሃብትን ጠብቆ ጥቅም ላይ ለማዋል በየዓመቱ በሚካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በሚሊዮን የሚቆጠር የሰው ኃይል በስራው እየተሳተፈ ይገኛል።

ነገር ግን በብዙ ቦታዎች ስራው ተጀምሮ ቀጣይ ተጨማሪ የጥገና ስራዎች ባለመሰራታቸው የሚፈለገው ያህል ውጤት እየተገኘ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ተከታታይነት ያለው ሥራ መስራት ከተቻለ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም አመልክተዋል።

ዶክተር ካባ እንዳሉት ሀገሪቱ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች ብትሆንም የእውቀት ማነስ፣ የመረጃ ክፍተት፣ የቴክኖሎጂና የቅንጅት መጓደል ያላትን ሃብት በአግባቡ እንዳትጠቀምበት አድርገው ቆይተዋል።

በቀጣይ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራውን ቀጣይነት ባለው መልኩ በማከናወን ሀገሪቱ ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን ሚኒስቴር መሰሪያ ቤቱ ከአጋር አካላት ጋር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የውሃና መሬት ሃብት ማዕከል ለአርሶ አደሩ የሚሰጣቸው የክህሎት ስልጠናዎችና የሚያደርገው ድጋፍ የመንግስት ጅምር ሥራዎችን ለማስቀጠል ጉልህ ሚና እንዳለውም አመልክተዋል።

"መረጃ ላይ ተመስርተን ስንሰራ ችግሩን ለይተን መፍትሄ ለመስጠት ያስችለናል" ያሉት ዶክተር ካባ የምርምር ተቋማት ችግሮችን ከመለየት ባለፈ ከነመፍተሄዎቻቸው ለተጠቃሚው ማድረስ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃና መሬት ሃብት ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ጌቴ ዘለቀ በበኩላቸው አንዳሉት ማዕከሉ በዘላቂ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ላይ ቴክኖሎጂዎችን ያወጣል፣ ይሞክራል፣ ሳይንሳዊ መረጃም ይሰጣል።

በሀገር ደረጃ ሁሉንም ቀጠናዎች የያዘ 15 የክትትል ማዕከሎች እንዳሉት ገልጸው በዘላቂ የመሬት አያያዝም በአባይ ተፋሰስ ውስጥ ሰባት ሞዴል የመማሪያ ተፋሰሶች ማዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

ዶክተር ጌቴ እንዳሉት ቴክኖሎጂዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አቅማቸውንና ዘላቂነታቸውን በማየት ለፖሊሲ አውጭውና ለተመራማሪዎች በሚያግዝ መልኩ ለመማሪያነት እያዋሉ ይገኛሉ።

ማዕከሉ የሀገሪቱ የተፈጥሮ ሃብት ሥራ የምርምር ማዕከል እንዲሆን ለማድረግና መረጃውንም ለተጠቃሚው ማድረስ የሚያስችል የኮምፒዩተር ሲስተም መዘርጋቱን አስረድተዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቦሰና ተገኘ በበኩላቸው የውሃና መሬት ሃብት ማዕከል ከክልሉ ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር ስድስት ሞዴል ተፋሰሶችን በአባይ ተፋሰስ ውስጥ ለይቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እነዚህ ተፋሰሶችም በባህር ዳር ዙሪያ በሰሜን ሜጫ፣ ደንበጫ፣ በይልማና ዴንሳና በደሴ ዙሪያ ወረዳዎች እንደሚገኙም አስረድተዋል።

በተከናወኑ ሞዴል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችም አመርቂ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቁመው በአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራዎች የለሙ አካባቢዎችን ሁሉም አካላት በባለቤትነት ሊጠብቀው እንደሚገባ አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ህዝብ እየተከናወኑ የሚገኙ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎችን አርሶ አደሩ አጠናክሮ እንዲቀጥል ቢሮው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና ዕገዛ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ማዕከሉ ካለፉት ስምንት ዓመታት ወዲህ ያከናወናቸውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ለማስተዋወቅ ባዘጋጀው የሁለት ቀናት ኮንፈረንስ ላይ ምሁራንና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም