ኖርዌይ በኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት መጠን የማሳደግ ፍላጎት አላት

117

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2011  ኖርዌይ በኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት መጠን የማሳደግ ፍላጎት እንዳላት በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር መረተ ሉንዴሞ ገለጹ።

አምባሳደሯ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ኢትዮጵያና ኖርዌይ የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ያላቸውና በተለያዩ ዘርፎች በጋራ የሚሰሩ አገራት ናቸው።

ይህን ትብብራቸውን የበለጠ ለማሳደግም ኖርዌይ በኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት መጠን የማሳደግ ፍላጎት አላት ብለዋል።

እንደ አምባሳደሯ ገለጻ አገራቸው በጾታ እኩልነት ላይ ጠንካራ አቋም ይዛ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ውጤታማ ሆናለች።

ይህን ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት የጾታ እኩልነትና ትምህርትን ማዳረስ ላይ ድጋፍ እያደረገች ነው።

በአሁኑ ወቅት የዓለም ስጋት በሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ኢትዮጵያ ታዳሽ ሃይል በመጠቀም ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች የተሻለ እየሰራች ነው ብለዋል።

አገራቸው የኢትዮጵያን አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት እየደገፈች መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያና ኖርዌይ ዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1947 ሲሆን ኖርዌይ ዋነኛ የልማት አጋር ብላ ከለየቻቸው አገራት ኢትዮጵያ አንዷ ናት።

ኢትዮጵያና ኖርዌይ በሰላምና ፀጥታ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በጾታ እኩልነት፣ በስደተኞች አስተዳደር፣ በትምህርትና በዘላቂ ልማት በትብብር ይሰራሉ።

''ኖርፈንድ'' የተሰኘው የአገሪቱ የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ በኢትዮጵያ የግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፍ እየሰራ ሲሆን፣ ያራ ኢንተርናሽናል የተባለው የኖርዌይ ማዳበሪያ አምራች ኩባንያ በአፋር ክልል የፖታሽ ማዕድን ፍለጋ ላይ ተሰማርቷል፡፡

ያራ ዳሎል ቢቪ በሚባል ስም ኢትዮጵያ ውስጥ ባቋቋመው እህት ኩባንያ አማካይነትም በ100 ሚሊዮን ዶላር የፖታሽ ማዕድን ፍለጋ ሥራ አከናውኗል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም