የአሜሪካ ብሔራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ የባለሙያዎች ቡድን የአውሮፕላን አደጋ በደረሰበት ስፍራ ምርመራ እያደረገ ነው

84

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2011 የአሜሪካ ብሔራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ የባለሙያዎች ቡድን የአውሮፕላን አደጋ ስፍራ ምርመራ እያደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ።

ከትናንት በስቲያ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር የነበረው ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ከቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው ጊምቢቹ ወረዳ ውስጥ መከስከሱ ይታወቃል።

የበረራ ቁጥሩ ኢቲ 302 የሆነው ይህ አውሮፕላን 149 መንገደኞችንና 8 የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ በረራ ከጀመረ ከስድስት ደቂቃ በኋላ በመከስከሱ በውስጡ የነበሩ 157 ሰዎች ህይወት አልፏል።

የአየር መንገዱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አስራት በጋሻው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአሜሪካ ብሔራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ የባለሙያዎች ቡድን ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ጋር በመሆን አውሮፕላኑ በተከሰከሰበት ስፍራ ምርምራ እያደረገ ይገኛል።

የቡድኑ በሁለት ተከፍሎ ትናንትና እና ዛሬ ኢትዮጵያ መግባቱንና በአደጋው ስፍራ በመገኘት አስፈላጊውን ምርምራና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለሙያዎቹ ብዛት ስንት እንደሆኑ አቶ አስራት የገለጹት ነገር የለም።

የአሜሪካ ብሔራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ የአውሮፕላን አደጋው በደረሰበት ቀን አራት አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን እንደሚልክ መግለጹ ይታወሳል።

የተከሰከሰው ቦይንግ 737 ማክስ 8 ሞዴል አውሮፕላን አምራች የሆነው ቦይንግ የምርምራ ቡድኑ አካል እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከትናንት በስቲያ ከአደጋው በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹም ይታወቃል።

የእስራኤል መንግስት በአደጋው ቦታ ከኢትዮጵያ ባለሙያዎች ጋር በመሆን የፎረንሲክ ምርመራ እያደረገ ሲሆን የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ "የኢትዮጵያ መንግስት በምርመራው ዙሪያ ለሚጠይቀን እርዳታ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን" በማለት ከአደጋው በኋላ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል።

የኢንዶኔዢያ መንግስትም ኢትዮጵያን በአውሮፕላን አደጋ ምርምራው ለመርዳት ዝግጁ መሆኗንም ገልጻለች።

የምርመራ ሂደቱን ያቀላጥፋል ተብሎ የሚታመንበት የአውሮፕላኑ የተለያዩ መሣሪያዎች እንቅስቃሴ መዝግቦ የሚያስቀረውን (DFDR) ወይም የመረጃ ሳጥን (balck box) አደጋው በደረሠበት ቦታ ትናንት መገኘቱ ይታወቃል።

በበረራ ወቅት የአብራሪዎቹን እና በአውሮፕላኑ ውስጥ ድምጾችን የሚቀርጸው መሣሪያ (CVR)  መገኘቱንም አየር መንገዱ ገልጿል።

የመረጃ ሳጥኑ መገኘት ለአደጋው መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ ለተባሉ ምክንያቶች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንዲገኝ እንደሚያደርግ የአቪዬሽን ባለሙያዎች በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም