ቦይንግ በ737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ላይ የሶፍትዌር ማሻሻያ እንደሚያደርግ አስታወቀ

735

መጋቢት 3/2011 የአሜሪካው ግዙፍ የአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ኩባንያ በ737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ላይ በሳምንታት ውስጥ የሶፍትዌር ማሻሻያ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ቦይንግ ይህን ያለው የአሜሪካ የአቪየሽን አስተዳደር ኩባንያው በሚያዚያ ወር በአውሮፕላኖቹ ላይ የዲዛይን ለውጥ እንዲያደርግ ሀሳብ ማቅረቡን ተከትሎ ነው።

ባለፈው ዕሁድ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን ጉዞ በጀመረ በስድስት ደቂቃ ውስጥ በመከስከሱ 157 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።


ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን

ቦይንግ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ በ737 ማክስ 8 አውሮፕላኑ ያጋጠመውን አደጋ ተከትሎ የደህንነት ስጋት ጥያቄዎች እየተሰነዘሩበት ነው።

ባለፈው ጥቅምት ወር ቦይንግ 737 ማከስ 8 አውሮፕላን ኢንዶኔዥያ ውስጥ ጉዞ በጀመረ በ13 ደቂቃ ውስጥ ተከስከሶ በውስጡ የነበሩ 189 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።

ቦይንግ አውሮፕላኖቹ የበረራ ደህንነታቸው አስተማማኝ ነው ቢልም፤ በርካታ ሀገራት ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ላልተወሰነ ጊዜ ከበረራ እያገዱ ነው።

የአሜሪካ የአቪየሽን አስተዳደር ኩባንያው በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖቹ ላይ የበረራ ደህንነቱን የሚያረጋግጡ የዲዛይን ለውጦችን እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ቦይንግ በበኩሉ ሶፍትዌር እያሻሻለ መሆኑን ገልጾ፥ በሳምንታት ውስጥ በሁሉም ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች እንደሚተገበር ጠቁሟል።

ምንጭ፦ሮይተርስ