በድሬዳዋ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ሰላምን ለማስፈንና የተሻለች አገር ለመገንባት የድርሻችንን እንወጣለን አሉ

78

ድሬዳዋ መጋቢት 3/2011 በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) አባላትና ደጋፊዎች ሰላምን ለማስፈንና የተሻለች አገር በመገንባት ድርሻቸውን  እንደሚወጡ ትናንት አረጋገጡ።

የድርጅቱ 44ኛ የምስረታ በዓል ተከብሯል።

የበዓሉ ተሳታፊዎች  በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በአገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና ለሕዝቦቿ የምትመች አገር በመገንባት ሚናቸውን ለመወጣት ይተጋሉ።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ ወጣት ፍቅሬ ገዳሙ አባቶች ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ የብሔሮች መብት መከበር የከፈሉትን መስዋትነት ወጣቱ ትውልድ  አገሩን በማልማት ሊያሳይ  ይገባዋል ብሏል፡፡

''የኢትዮጵያ ሕዝቦች መፋቀርና አንድነት እንጂ ጦርነት አያስፈልገንም ፤ ካለፈው ጦርነት መማር መቻል አለብን'' ሲልም ተናግሯል፡፡

የድርጅቱ ደጋፊዎችና አባላት በአገሪቱ ብልጽግና እንዲመጣ ሌት ተቀን እንሰራለን ያለችው ደግሞ ወይዘሮ መስከረም ተክለኃይማኖት ናቸው።

ልዩነቶችን በማክበርና አንድነትን በመጠበቅ የተሻለች አገር መገንባት የአሁኑ ትውልድ ወቅታዊ አጀንዳ መሆን እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

አቶ ሐብታሙ ኪሮስ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው የፖለቲካ እሰጣ እገባ ዘመን የተሻገረውን የሕዝቦች ለዘመናት የቆየ መስተጋብር ሊያደበዝዘው እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡

በተለይ ወጣቱ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን የማሰራጩትን መረጃዎች በአግባቡ በማጥራትና በመረዳት አገራዊ አቋሙንና አንድነቱን ማጠናከር እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡

አቶ ኃይለማርም ተክሌ አዲሱ ትውልድ አገሪቱን ከድህነት በማላቀቅ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡

''ሁላችንም አንድ ሆነን ቀን ከሌሊት መስራትና ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ አለብን'' ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን የአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን ወኔና ጥንካሬ በመላበስ ሰላም በማስፈንና ብልጽግና በማምጣት  መስራት እንደሚገባው አስታውቀዋል፡፡

በተለይ በአገሪቱ የተጀመረው ሁሉን አቀፍ ለውጥ  ለማሳካት ሁሉም ድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች አመራሮች የድጋፍ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም