የአልጄሪያ ፕሬዚዳንት ለ5ኛ ጊዜ የመወዳደር እቅዳቸውን ሰረዙ

93

መጋቢት 3/2011  የአልጄሪያ ፕሬዚዳንት አብደላዚዝ ቦተፍሊካ በሀገሪቱ በመጪው የፈረንጆቹ ሚያዚያ 18 እንደሚካሄድ የሚጠበቀውን ምርጫ እንዲራዘም ውሳኔ ሰጥተዋል።

“በምርጫው አልወዳደርም፤ አዲስ የአልጄሪያ ሪፐብሊክ እንዲመሰረት ነው በቀጣይ የምስራው” ብለዋል።

ፕሬዚዳንት አብደላዚዝ ዘንድሮ በሚካሄደው መርጫ እንደሚወዳደሩ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ላለፉት ሳምንታት ያለማቋረጥ ህዝባዊ ተቃውሞ አጋጥሟቸዋል።

አልጀሪያን ለ20 ዓመታት የመሯት ቦተፍሊካ፥ ከፈረንጆቹ 2013 ጀምሮ በስትሮክ ህመም እየተሰቃዩ አበዛኛውን ጊዜያቸውን በህክምና ነው የሚያሳልፉት።

የ82 ዓመቱ ቦተፍሊካ የሚያዚያው ምርጫ እንደሚራዘም ቢወስኑም መቼ እንደሚካሄድ ቀነ ገደብ አልተቀመጠለትም።

በሀገሪቱ አዲስ የካቢኔ ሹም ሽር እንደሚካሄድም እየተነገረ ነው።

ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን ይወርዳሉ ወይስ አይወርዱም የሚለው እስካሁን ባይታወቅም የአልጀሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር አህመድ ኦያሂያ በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።

ኦያሂያ በሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ ኑረዲን ቤዱይ የተተኩ ሲሆን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም አዲስ ካቢኔ እንደሚያዋቅሩ መረጃዎች ወጥተዋል።
ምንጭ፦ቢቢሲ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም