በአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት ስራዎች ተጠቃሚ ሆነናል...የትግራይ አርሶ አደሮች

60

አክሱም መጋቢት 2/2011 ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት ሥራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን የትግራይ ማዕከላዊ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።

አርሶ አደሮቹ ለኢትዮዽያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው ለተቀናጀ የግብርና ሥራ ያለው ጠቀሜታ የጎላ  ነው።

ካለው ተጨባጭ ጥቅም በመነሳት በየዓመቱ ለ20 ቀን ነጻ የጉልበት አስተዋጽኦ በማድረግ ልማቱን እያከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዞኑ ታሕታይ ማይጨው ወረዳ አዲጓራ ቀበሌ የሚኖረው ወጣት አረሶ አደር ተወለ በየነ ባለፉት ዓመታት በአካባቢያቸው በተሰሩ የአፍርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ተጠቃሚ መሆኑን ተናግሯል።

በአካባቢው በለማ ተራራ ላይ ከሌሎች አራት ጓደኞቹ ጋር በመሆኑን በንብ ማነብ ስራ ላይ መሰማራቱን የገለጸው ወጣቱ በአራት ዘመናዊ የንብ ቆፎ በጀመሩት የማር ምርት ሥራ ከ30 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ገልጿል።

የማር ምርቱ የገበያ አዋጭነት እንዳለው የጠቆመው ወጣት ተወለ 30 ዘመናዊ የንብ ቆፎዎችን ለመግዛት በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ተናግሯል።

በዞኑ በመረብለኸ ወረዳ የአሳይመ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ካሕሳይ አብርሃለይ በበኩሉ በአፍርና ውሃ ጥበቃ ስራው ከለሙ አካባቢዎች በቂ የከብት መኖን በማጨድ ለእንስሳት እርባታና ማድለብ ሥራ ምቹ እድል እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

የልማት ሥራው ከዓመታት በፊት ደረቃማ የነበሩ ስፍራዎችም እርጥበት እንዲቋጥሩና የከባቢ አየር እንዲጠበቅ ማስቻሉንም ገልጸዋል።

የተፋሰስና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራው ለመስኖ ስራቸው አጋዥ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዞኑ ላዕላይ ማይጨው ወረዳ ዱራ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ብርሃነ ወልደአረጋይ ናቸው።

ከመሰኖ ስራ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ በአጭር ጊዜ ካለሙት የመጀመሪያ ዙር የመስኖ ልማት 12 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የዞኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና መስኖ ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ኃይለማርያም ወልደገብርኤል  በክልል ደረጃ የተያዘውን ጎርፍ አልባ የተፋሰስ ልማት ስኬታማ ለማድረግ  በግብርና ባለሙያዎች የታገዘ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

በዘንድሮ በጀት ዓመት በዞኑ 280 ሺህ አርሶ አደሮች የተሳተፉበት የ20 ቀናት ነጻ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል።

በመካሄድ ላይ ባለው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት ስራም በ14 ሺህ 300 ሄክታር መሬት የድንጋይና አፈር እርከን እንዲሁም በ378 ተፋሰሶች ላይ የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

ባለፉት ዓመታት በዞኑ ውስጥ በተከናወነ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በተለያዩ ምክንያቶች ተራቁቶ የነበረ 103 ሺህ ሄክታር መሬት አገግሞ  በደን ሙሉ በሙሉ መሸፈኑን ገልጸዋል።

በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በለሙ አካባቢዎችም ከ9 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችና ወጣቶች በንብ ማነብ፣ በመስኖ ልማትና በእንስሳ ማድለብ ሥራዎች ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆናቸውን ከዞኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና መስኖ ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም