ለአዲግራት ሆስፒታል በ30 ሚሊዮን ብር የተገነባው የሕክምና መስጫ ሕንጻ ለአገልግሎት ተዘጋጀ

505

መቀሌ መጋቢት 2/2011 አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ30 ሚሊዮን ብር ወጪ ለአዲግራት ሆስፒታል ያስገነባው ተጨማሪ የሕክምና መስጫ ሕንጻ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ተዘጋጀ።

በሦስት ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈው ባለ አንድ ፎቅ ዘመናዊ ሕንጻ በትግራይ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ተመርቋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በእዚህ ወቅት እንዳሉት በከተማው ከጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለማሻሻል ሕንጻው የራሱ አስተዋጽኦ አለው።

ዩኒቨርሲቲው በማስተማሪያነት የሚጠቀምበት ሆስፒታል ያለበትን ችግር ተገንዝቦ ተጨማሪ ሕንጻ ማስገንባቱ ከህዝብ ጋር ያለውን የቆየ መልካም ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያግዘውም ተናግረዋል።

በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ጋይም ገብረስላሴ በበኩላቸው፣ ” የሕንጻው መገንባት በሆስፒታሉያለውንየሕክምና መስጫ ክፍል እጥረት ለማቃለልና ተግባራዊ ትምህርት ለመስጠት ያስችላል” ብለዋል።

ቀደም ሲል በሆስፒታሉ በነበረ የክፍል ጥበት ምክንያት ለህክምና ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት ለመስጠት ችግር እንደነበር አስታውሰዋል።

ሕንጻው የተሟላ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የዩኒቨርሲቲው የሕክምና ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን በተግባር  እንዲቀስሙ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ዲኑ አመልክተዋል።

ሕንጻው የሕክምና መሳሪያዎች ተሟልተውለት ሕብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት ማግኘት እንዲችል የባለድርሻ አካላት ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑንም ዶክተር ጋይም ተናግረዋል።

እንደዶክተር ጋይም ገለጻ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃው ዘመናዊ ሕንጻ 157 መኝታ አልጋዎችን የመያዝ አቅም አለው።

ከእዚህ በተጨማሪ አራት የቀዶ ሕክምና ክፍሎችን ጨምሮ የማዋለጃና የእናቶችና ሕፃናት ሕክምና መስጫ ክፍሎችን አካትቶ የያዘ ነው።

የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ሃደራ በበኩላቸው፣ የአዲግራት ሆስፒታል በ1967 ዓ.ም ለ15 ሺህ ህዝብ እንዲያገለግል ታስቦ መገንባቱን አስታውሰዋል።

“በአሁኑ ወቅት ከትግራይ ምስራቃዊ ዞን አልፎ ከአጎራባች የዓፋር ክልል ወረዳዎችና በአቅራቢያው የሚመጡ ኤርትራዊያንን ጨምሮ ከ1 ሚሊዮን 300 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል” ብለዋል።