የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ

627

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2011 የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ ።

ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አህመድ ጋር በሁለትዮሽ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ፕሬዚዳንት ማክሮን በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እንደሚጎበኙም የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመረጃው ጠቅሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር  አብይ ባለፈው ጥቅምት 19 እና 20/  2011 ዓ.ም በፕሬዚዳንት ማክሮን በተደረገላቸው ግብዣ በፈረንሳይ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

በጉብኝታቸውም ከፕሬዚዳንት ማክሮን ጋር የሁለቱን አገሮች ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ፈረንሳይ በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የተጋረጠውን ችግር ለመፍታት ድጋፍ  እንደምታደርግም ፕሬዝዳንቱ ቃል ገብተው ነበር።

በሰላም፣ በዴሞክራሲና በልማት ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ውይይት በማድረግ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ለማዘመንና የሰው ኃይል በማሰልጠን ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ ድጋፍ እንደምታደርግም ስምምነተ ማድረጋቸው ይታወቃል።

በኢኮኖሚው ረገድ በአየር መንገድ አገራቱ ያላቸውን ስምምነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና ከ100 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ወጭ በማድረግ የአዲስ አበባን ኤርፖርት ለማዘመን ፈረንሳይ እንደምትደግፍም እንዲሁ።

ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚው ማሻሻያ ከዓለም ባንክ ከምታገኘው የበጀት ድጋፍ በተጨማሪ ፈረንሳይ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ፕሬዝዳንት ማክሮን አረጋግጠዋል።

ፕሬዝዳንቱ በነገው እለት በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያና ፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እ.አ.አ በ1897 መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።