የአገሪቷን የፋይናንስ ስርዓት ችግሮች በመለየት መፍትሄ የሚያመላክት ጉባዔ መካሄድ ጀመረ

509

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2011 የአገሪቷ የፋይናንስ ስርዓት ያሉበትን ችግሮች በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል የተባለ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ኮሚዩኒቲና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በመተባበር ያዘጋጁት ጉባዔ ከዛሬ ጀምሮ እስከ መጪው አርብ ይካሄዳል።

የማህበሩ መስራች ወይዘሪት ቤዛ እሸቱ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት የውይይቱ ትኩረት በአገሪቱ ያለው የፋይናንስ ስርዓት ያሉበትን ክፍተቶች በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ነው።

የጤና፣ የፋይናንስ፣ የዲፕሎማሲ፣የትምህርት፣ የውሃ ሃብት አጠቃቀምና የአይሲቲን አሰራር በሚመለከትም ውይይት ይካሄዳል ብለዋል።

ጉባኤው የፋይናንስ አስተዳደር፣ የጤና፣ የዲፕሎማሲ፣ አይቲ ቴክኖሎጂ ላይ ከፍተኛ የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት መሆኑን የጠቆሙት ደግሞ የቡድኑ መሪ ዶክተር ተፈራ በየነ ናቸው።

የቡድኑ አባላት ልምዱን ባጋራበት ዘርፍ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ከለዩ በኋላ ምክረ ሃሳብቦችን እንደሚያቀርቡም አረጋግጠዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በአገሪቷ በተለይ በፋይናንስ ዘርፉ ብክነት መኖሩን ተናግረዋል።

በመሆኑም በአሜሪካ ትልልቅ ቦታዎች ላይ ለብዙ ዓመታት ሲሰሩ የነበሩት ባለሙያዎች ልምዳቸውን ማጋራታቸው ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ እግዛ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ባህል ብዙም ያልተለመደ በመሆኑ በተለይ በፋይናንስ፣ በአይሲቲ፣ በጤና፣ በትምህርትና ሌሎችም ተቋማት አሰራርን ማዘመን እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።

በቀጣይም ቡድኑ የሚሰጠውን ግብአት በመጠቀም አሰራሮችን የማሻሻል ስራ ተግባራዊ እንደሚደረግ ሚንስትሩ አረጋግጠዋል።

የጉባኤው አባላት ከሰሜን አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ይህንን ሞያዊ እገዛ ለማድረግ የፈቀዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በአሜሪካ በነበራቸው ጉብኝት ለአገራቸው ድጋፍ እንዲያደርጉ በጠየቁት መሰረት ነው።

ጉባዔ ከዛሬ ጀምሮ እስከ መጪው አርብ እንደሚካሄድ የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።