ካሳና ተለዋጭ ቦታ ሳይሰጠን ቤታችን ፈርሶብናል---በመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች

59

መቀሌ መጋቢት 2/2011 ዓ.ምካሳና ተለዋጭ ቦታ ሳይሰጣቸው ከ12 ዓመት በላይ የኖሩበት ቤት እንደፈረሰባቸው በመቀሌ ከተማ የዓዲ ሓቂ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የዓዲ ሓቂ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ለነዋሪዎቹ ካሳና ተለዋጭ ቦታ ያልተሰጠው ህጋዊ የቤት ይዞታ ማረጋገጫ ስለሌላቸው መሆኑን  አስታውቋል።   

በመቀሌ ከተማ የዓዲ ሓቂ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ለኢትዮዽያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት አካባቢያቸው ወደ ከተማ ክልል ከመግባቱ በፊት በእንደርታ ወረዳ ደብረገነት ቀበሌ ገበሬ ማህበር ይተዳደሩ ነበር፡፡

ከመቀሌ ከተማ ወደ ኢንዱስትሪ ፓሪክ ለሚወስደው የአስፓልት መንገድ ለዓመታት ከኖሩበት መኖሪያ ቤት ቢነሱም ካሳና ተለዋጭ ቦታ ሳይሰጣቸው መኖሪያ ቤታቸው እንዲፈርስ መደረጉ አግባብነት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

የክፍለ ከተማው ነዋሪ አቶ ተስፋይ ገብረ እንደተናገሩት ያለምንም የማፍረሻ ትዛዝና ማስጠንቀቂያ ቤታቸው እስከንብረቱ  እንዲወድም ተደርጓል።

በክፍለ ከተማው ከሳና ተለዋጭ ቦታ ይሰጣችኋል ተብሎ ቃል መገባቱን ያስታወሱት ነዋሪው ቃል የተገባው ተፈጻሚ ሳይሆን የእሳቸውን ጨምሮ የ50 ነዋሪዎች ቤት መፍረሱን ተናግረዋል፡፡

በአከባቢው ከ12 ዓመት በላይ መኖራቸውን የገለጹት ወይዘሮ እምበይቱ ሓድስ በበኩላቸው "አፍርሱ የሚል ወረቀት ሳይሰጠን ቤታችን እንዲፈርስ መደረጉ ህጋዊ አይደለም" ብለዋል።

ወይዘሮ  ሕይወት ባህታ በበኩላቸው ያለ አግባብ ቤታቸው እንዲፈርስ በመደረጉ ልጆችና የቤት እንስሶቻቸውን ለማኖር መቸገራቸውን  ገልጸዋል።

የዓዲ ሓቂ ክፍለ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማይ ገብረ በበኩላቸው ነዋሪዎች ቤታቸው እንዲፈርስ የተደረገው ህግን ያልተከተለ የመሬት ግዢ በማከናወናቸው መሆኑን አመልክተዋል።

በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ምክንያት ለሚነሱ ነዋሪዎች ቀድሞ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጣቸው እንዲነሱ መደረጉ የማዘጋጃ ቤቱ ስህተት መሆኑን አምነዋል።

" ቤቶቹን የማፍረስ እርምጃ የወሰድነው ፈጥነን ወደ ልማት ለመግባት ሲባል ነው " ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የዓዲሓቂ ክፍለ ከተማ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ገብረሚካኤል ገብረመድህን በበኩላቸው ወደ መቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሚወስድ የአስፋልት መንገድና የባቡር ሀዲድ ግንባታ ምክንያት እስካሁን 177 ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቦታቸውና ከእርሻቸው እንዲነሱ መደረጉን አስታውቀዋል።

በልማቱ ለሚነሱት የሚከፈለው ካሳ በተለያዩ ምክንያቶች መጓተቱን የገለጹት ምክትል አስተዳዳሪው፣ እስካሁን ለ128 ነዋሪዎች የካሳ ክፍያ መፈፀሙን አመልክተዋል።

አቶ ገብረሚካኤል እንዳሉት የካሳ ክፍያ የተፈጸመላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ያላቸው ናቸው።

"በምሪት፣ በስጦታና በግዢ መኖሪያ ቤት ያላቸው ነዋሪዎች የመሬት ካሳና ተለዋጭ ቦታ እንዲያገኙ ተደርጓል" ብለዋል።

ከህግ ውጭ መሬት ወረው የጨረቃ ቤት ለሰሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ምትክ ቦታ ለመስጠትና ካሳ ለመክፈል መመሪያው እንደማይፈቅድም አስረድተዋል።

ህጋዊ ያልሆነ ቦታ ይዘው እንዲነሱ የተደረጉ የሕብረተሰብ ከፍሎች የት መኖር እንዳለባቸው አስተዳደራዊ መፍትሄ ለመስጠት ከሚመለከታቸው  የዞንና የክልል የሥራ ኃላፊዎች ጋር ምክክር እየተደረገ መሆኑን አቶ ገብረሚካኤል ተናገረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም የነዋሪዎችን ቅሬታ በዘገበበት ወቅት ክፍለ ከተማው እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ እልባት እንደሚሰጣቸው ቃል ቢገባም እስካሁን ተግባራዊ አለማድረጉ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም