የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ተካሂደዋል

71

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2011 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ስምንተኛ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ተካሂደዋል።

ትናንት መቐለ ላይ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ መቐለ ሰብዓ እንደርታን 29 ለ 23 ጎንደር ላይ ከምባታ ዱራሜ ጎንደር ከተማን 29 ለ 22 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከቡታጅራ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 29 ለ 29 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ለሶስተኛ ጊዜ አቻ የወጣ ሲሆን ከዚህ በፊት ከመቐለ ሰብዓ እንደርታና ከምባታ ዱራሜ ጋር ያደረገውን ጨዋታ በአቻ ውጤት ማጠናቀቁ ይታወሳል።

በስምንተኛ ሳምንት መርሃ ግብር የሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማና መከላለያ ጨዋታ ባለማድረጋቸው አራፊ ክለቦች ናቸው።

በሌላ በኩል በሁለቱም ጾታዎች የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ተካሄደዋል።

በኢትዮጵያ ወንዶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በምድብ አንድ ትናንት አዳማ ላይ ሀዋሳ ከተማ ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርትን 60 ለ 55 ከትናንት በስቲያ ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት አዳማ ከተማን 61 ለ 57 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።

በዚሁ ምድብ አርብ የካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም  አዳማ ላይ በተካሄደ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ አዳማ ከተማን 67 ለ 49 በሆነ ውጤት ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ትናንት በወንዶች ምድብ ሁለት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ወልቂጤ ከተማ ጎንደር ከተማን 60 ለ 55 ከትናንት በስቲያ በራስ ሃይሉ ስፖርት ማዕከል ጎንደር ከተማ የካ ክፍለ ከተማን 64 ለ 58 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።

አርብ የካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም በዚሁ ምድብ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ የካ ክፍለ ከተማን 64 ለ 53 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።

በተያያዘም የኢትዮጵያ ሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የምድብ ሁለት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ተካሄደዋል።

ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ጎንደር ከተማ ሀዋሳ ከተማን 53 ለ 47  ከትናንት በስቲያ በራስ ሃይሉ ስፖርት ማዕከል ጎንደር ከተማ ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽንን 57 ለ 52 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በዚሁ ምድብ አርብ የካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም በተደረገ ጨዋታ ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሀዋሳ ከተማን 59 ለ 39 ማሸነፉ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን አዲስ የውድድር ፎርማት መሰረት በወንዶችና በሴቶች በተመሳሳይ በምድብ ሁለት እንዲሁም በወንዶች በምድብ አንድ የሚገኙ ክለቦች በቅደም ተከተል ወደ አዲስ አበባና አዳማ በማቅናት ለሶስት ተከታታይ ቀናት እርስ በርስ ጨዋታቸውን አድርገዋል።

በተጨማሪም ትናንት በሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ ተስተካካይ ጨዋታ ወላይታ ድቻ በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም መከላከያ ከወላይታ ድቻ ከጠዋቱ ሶስት ሰአት ተስተካካይ ጨዋታቸውን ካደረጉ በኋላ የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም